አብዱልከሪም ንኪማ በይፋ ባህር ዳርን ተቀላቅሏል

ከቀናት በፊት በሶከር ኢትዮጵያ ባህር ዳርን ለመቀላቀል መስማማቱን ዘግበን የነበረው ቡርኪናፋሶዋዊው ተጫዋች የጣና ሞገዶቹን ተቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ቡርኪናፋሶዋዊው የአጥቂ አማካይ አብዱልከሪም ንኪማን ለማስፈረም መስማማቱን ከቀናት በፊት ዘግበን እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ተጫዋቹም በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ በመምጣት ዝውውሩን ማገባደዱ ይፋ ሆኗል።

በ2009 እና 2010 በቅዱስ ጊዮርጊስ በመጫወት ከኢትዮጵያ የእግርኳስ አፍቃሪያን ጋር የተዋወቀው ንኪማ ከኬንያው ጎር ማህያ ጋር ቀሪ በአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም በስምምነት በመለያየት ውሃ ሰማያዊውን መለያ ለመልበስ በዛሬው ዕለት የሁለት ዓመት ፊርማውን አኑሯል። መስከረም 3 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ተገልጾ የነበረው ተጫዋቹም ከቤተሰብ ችግር ጋር በተያያዘ ፍቃድ ጠይቆ የመምጫው ቀኑ እንደተገፋ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አብዱልከሪም ንኪማም የባህር ዳር ከተማ የክረምቱ የዝውውር መስኮ የመጨረሻው ፈራሚ መሆኑ ተጠቁሟል።