ወንድወሰን ገረመው ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰበትን ዝውውር ፈፅሟል

በተለያዩ ውድድር መድረኮች ዋንጫዎችን በማንሳት የሚታወቀው ግብ ጠባቂ አዲስ አዳጊውን ክለብ ተቀላቅሏል፡፡

ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ ግብ ጠባቂ በይፋ አስፈርሟል፡፡ ወንድወሰን ገረመው ከሦስት ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰበትን ዝውውር መፈፀሙንም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

2003 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ በመቀጠል ወደ ወላይታ ድቻ በማምራት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያሳካው ግብጠባቂው በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በወላይታ ድቻ የነበረው አስገራሚ ጉዞ ላይ የሚወሳ ሲሆን በመቀጠል በከፍተኛ ሊጎቹ ኤሌክትሪክ እና ስልጤ ወራቤ እንዲሁም የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ደግሞ በአንደኛ ሊጉ በቡራዩ ከተማ በመጫወት ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዲያድግ በተደጋጋሚ ፍፁም ቅጣት ምቶችን በማዳኑ ተጠቃሽ ነበር።