ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

በሀዋሳ ከተማ ዝግጅት እየሰሩ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች የሙከራ ዕድል ከተሰጧቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱን አስፈርመዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ2014 ዝግጅትን እየሰሩ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው እየቀላቀሉ የሚገኙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ለሁለት ሳምንታት በሙከራ ሲመለከቷቸው ከነበሩ ከ15 በላይ ከድሬዳዋ እና አካባቢዋ የመጡ ተጫዋቾች መካከል አሰልጣኙ አመርቂ እንቅስቃሴን አሳይተዋል ያሏቸውን ሁለት ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ መቀላቀላቸውን ክለቡ አስታውቋል።

በድሬዳዋ የተለያዩ የውስጥ ውድድሮች ሲጫወት የነበረው እና በድሬዳዋ ከተማ ተስፋ ቡድን ከ2009 ጀምሮ ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ አብዱልፈታህ ዓሊ እና በድሬዳዋ ከተማ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች ከተጫወተ በኋላ ያለፈውን አመት በአንደኛ ሊጉ ድሬዳዋ ፖሊስ የተጫወተው ተከላካዩ አቤል አሰበ የተሰጣቸውን የሙከራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ዋናውን ቡድን ተቀላቅለዋል፡፡