አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ ይፋ ሆኗል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የትጥቅ አጋር የሆነው ኡምብሮ ለቡድኖቹ ያመረተውን አዲስ ትጥቅ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።

2019 ላይ በተለያየ እርከን ለሚገኙ የወንድ እና ሴት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች የመጫወቻ እንዲሁም የመለማመጃ ትጥቅ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተስማማው አምብሮ በቅርቡ ለአራት ዓመታት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሱ ይታወቃል። እንግሊዝ ላይ መቀመጫውን ያደረገው አምብሮ በኮቪድ-19 ምክንያት ያለፉትን ጊዜያት በታሰበው መልኩ ትጥቁን ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማቅረብ ባይችልም በቅርቡ በተስማማው አዲስ ውል መሠረት ለዚህ ዓመት ያዘጋጀውን ትጥቅ አስረክቧል። ከቀናት በፊት አዲስ አበባ የደረሰው ትጥቅም ዛሬ አመሻሻሽ ለብዙሃን መገናኛ አባላት ይፋ ሆኗል።

በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል በተካሄደው መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና የሥራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች እና ተጫዋቾች ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ተገኝተዋል። በቅድሚያም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ከጉምሩክ ጋር ተያይዞ በነበረ ችግር ዝግጅቱ 35 ደቂቃዎችን በመዘግየቱ ይቅርታ ጠይቀው ስለ ትጥቆቹ ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል።
“የነበርንበት ጊዜ የኮቪድ ችግር ስለነበር መዘግየቶች ነበሩ። አምብሮዎች የአንድ ዓመት ብለው በላኩልን ትጥቅ ነበር ሦስት ዓመታት የተጠቀምነው። ከዚህ በተጨማሪ ከዶላር ምንዛሬ ጋርም ተያይዞ ችግሮች ነበሩ። የዚህ ትጥቅ ዲዛይን በራሳችን ነው የተሰራው። ሀገራዊ ይዘት እንዲኖረው አድርገናል። ከዚህ በተጨማሪም ትጥቁ ጥራቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲመረት አድርገናል።

“ከብሄራዊ ቡድኖቹ ትጥቆች በተጨማሪ 10 ሺ የደጋፊዎች መለያ አስገብተናል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መለያዎቹን የማከፋፈል መብቱን ሙሉ ለሙሉ አግኝተናል። የአዕምሮ ንብረት ሄደን ፍቃድም ወስደናል። ከዚህ በኋላ ያለ ፍቃድ ሱቅ ውስጥ የሚሸጥን ሰው የመጠየቅ መብቱ አለን። ስለዚህ ብራንዳችንን የመጠበቅ ሀላፊነት አለብን። አንድ ሰው ከአምስት መለያ በላይ እንዳይገዛም እየሰራን ነው።” በማለት ሁሉንም የትጥቅ አይነቶች ዲዛይን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች እያሳዩ ካብራሩ በኋላ ደጋፊዎች አንድን መለያ የሚገዙት በ1 ሺ ብር እንደሆነ ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ ጨምረው “ለወንዱ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ቡድኖቻችን ማልበስ የሚችል አቅም ላይ እንገኛለን። ከቱታዎቹ ውጪ ሁሉም የትጥቅ አይነቶች ስቶር ገብተዋል። ቱታውም የቁጥር ስህተት መጥቶ ነው ስቶር ያልገባው። ከነገ ጀምሮ ብሔራዊ ቡድናችን ትጥቁን መውሰድ ይችላል።” በማለት ሀሳባቸውን ከቀጠሉ በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ የተለየ መለያ ለማሰራት ከአምብሮ ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከአቶ ኢሳይያስ ገለፃ በኋላ መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት በየተራ እየለበሱ የመጡትን ትጥቅ ማስተዋወቅ ጀምረዋል። በቅድሚያም የሉሲዎቹ ተጫዋቾች ቡርትካን ገብረክርስቶስ፣ እፀገነት ብዙነህ እና መስከረም ካንኮ ሁለት አይነት የመዐድ ሰዓት ቲሸርቶች እና የልምምድ መለያዎችን ለብሰው አስተዋውቀዋል። በመቀጠል ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቪዲዮ ተንታኝ ኤልሻዳይ ቤኬማ የተዘጋጀውን ሁለት አይነት የደጋፊዎች መለያዎች ይፋ አድርጓል።

በመጨረሻም ለደቡብ አፍሪካው የደርሶ መልስ ጨዋታ የተሰባሰቡት የዋልያዎቹ ስብስብ አባል የሆኑት መናፍ ዐወል፣ ጌታነህ ከበደ፣ መስዑድ መሐመድ እና ጀማል ጣሰው ዋናው ቡድን የሚጠቀምበትን ሦስት አይነት አማራጭ መለያዎች በመልበስ አስተዋውቀዋል።

አጠር ያለ ጊዜ የፈጀው ሥነ-ስርዓት ሊገባደድ ሲል የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ለደጋፊዎች የተዘጋጁት 10 ሺ መለያዎች ከሚቀጥለው ረቡዕ ጀምሮ በይፋ መሸጥ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።