አዲስ አበባ ከተማ ተከላካዩን ዳግም አግኝቷል

በዘንድሮ የዝውውር መስኮት ወደ ጅማ አባ ጅፋር አምርቶ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማው ተከላካይ ዳግም ቡድኑን ተቀላቅሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ ጋር በከፍተኛ ሊግ መልካም የወርድድር ጊዜ ያሳለፈው ኢያሱ ለገሠ በቅድመ ስምምነት ጅማ አባ ጅፋርን በመቀላቀል በቢሸፍቱ ከተማ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል። ሆኖም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር እስከ ጥቅምት 30 ድረስ የሚያቆየው ኮንትራት ያለው በመሆኑ እና አዲስ አበባዎች ኢያሱ ከቡድናቸው ጋር እንዲቆይ ካላቸው ፍላጎት ጋር ተያይዞ መልቀቂያ ሳይሰጡት በመቅረታቸው የጅማ አባጅፋር ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል።

በዚህ ምክንያት ዳግመኛ ወደ ቀድሞ ክለቡ የመመለስ ግዴታ ውስጥ የገባው ኢያሱ በዛሬው በመዲናዋ ዋንጫ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ምንም እንኳን ከ18ቱ ውጪ ቢሆንም የቡድኑ አባል ሆኖ ተመልክተነዋል።