የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ውሎ

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ፍፃሜያቸውን ሲያገኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ተያይዘው አልፈዋል። ፋሲል ከነማ ደግሞ ቀድሞ መውደቁን ባረጋገጠው አዳማ ተሸንፏል።

አዳማ ከተማ 4-1 ፋሲል ከነማ

ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በጊዜ ግብ ማስተናገድ ጀምሯል። ጨዋታውን በጥሩ መነሳሳት የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች በ4ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ ያገኙትን የቅጣት ምት በበረከት ደስታ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረውት መሪ ሆነዋል። በተቃራኒው ወደ ጨዋታው ለመመለስ በቶሎ ተግቶ መጫወት የጀመሩት አዳማዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም አቡበከር ወንድሙ ከዳዋ ሁቴሳ የተቀበለውን ኳስ ቴዎድሮስ ጌትነት መረብ ላይ አሳርፎታል።

ወዲያው አቻ ከሆኑ በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የቻሉት አዳማዎች በ22ኛው ደቂቃ ሚሊዮን ሠለሞን ከቀኝ መስመር ባሻማው እና ዳዋ በግንባሩ ለማስቆጠር በሞከረው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር። ፋሲሎች በበኩላቸው ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም ሌላ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ እስከ 33ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። በዚህ ደቂቃም የግቡ ባለቤት በረከት ሌላ የቅጣት ምት አግኝቶ ዳግም ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ነበር። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ35ኛው ደቂቃ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ግብ ለማድረግ ጥረው መክኖባቸዋል። በቀኝ መስመር ወደ ፋሲል የግብ ክልል ያመሩት አዳማ ከተማዎች ደግሞ በአቡበከር አማካኝነት ወደ ጎል የመቱትን ኳስ የዐፄዎቹ የመሐል ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ኳሱን እመልሳለው ሲል ተጨርፎ መረብ ላይ አርፏል።

ከምድቡ ለማለፍ የግድ ሦስት ነጥብ የሚያስፈልጋቸው (የባህር ዳር ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ) ፋሲሎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ፍሬያማ ለማድረግ መታተር ይዘዋል። በተለይ በ58ኛው ደቂቃ በረከት ከወደ ግራ ያገኘውን ኳስ በመሞከር ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር። በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንካራ የነበሩት አዳማዎች በ65ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሦስት አሳድገዋል። በዚህም በቀኝ መስመር ራሱን ነፃ አድርጎ ሲጠብቅ የነበረው አቡበከር ፈጥኖ በመውጣት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ አሜ መሐመድ ደርሶ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

የጨዋታው መገባደጃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የታተሩት አዳማዎች ጥሩ ሲንቀሰቀቀስ በነበረው አቡበከር እና ዳዋ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። በ82ኛው ደቂቃ ደግሞ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ ግብ በማምራት ዳዋ የመታውን ኳስ የግብ ዘቡ ቴዎድሮስ ሲመልሰው አሜ አግኝቶት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ አራተኛ ግብ አድርጎታል። ጨዋታውም በአዳማ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው አዳማ ካስቆጠራቸው አራት ጎሎች ሦስቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው አቡበከር ወንድሙ የመርሐ-ግብሩ ኮከብ ተብሎ ተሸልሟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታም እንደ መጀመሪያው ፍልሚያ ግብ ለማስተናገድ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። በዚህም ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ፀጋዬ መላኩ በጥሩ ብቃት መረብ ላይ አሳርፎት ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሆነዋል። ገና በጊዜ መሪነት የተወሰደባቸው ባህር ዳር ከተማዎች በቶሎ አቻ ለመሆን ኳሱን ይዞ በመጫወት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ማምራት ይዘዋል። በተለይ ደግሞ በ15ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተገኘን የመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ወደ ሳጥን ሲሻማ የደረሰው ግርማ ዲሳሳ ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር። በ23ኛው ደቂቃ ደግሞ አብዱልከሪም ንኪማ ከሳጥን ውጪ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው ያለው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከኳስ ጋር ጊዜ ባያሳልፉም በሚያገኟቸው ጥቂት አጋጣሚዎች የሰላ ጥቃት እየፈፀሙ ይመለሳሉ። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ ከቆመ አጋጣሚ የተሻገረን ኳስ የመሐል ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ አግኝቶት ግብ አስቆጥሯል። ሁለተኛ ግብ ቢያስተናግዱም ተስፋ ያልቆረጡት ባህር ዳሮች በ33ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ቅብብል ፈረሰኞቹ የግብ ክልል ደርሰው በአፈወርቅ ኃይሉ አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ መሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ሊያስቆጥሩ ጥረው መክኖባቸዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ግን የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ፀጋዬ የባህር ዳር ተከላካይ ፈቱዲን የተሳሳተውን ኳስ አግኝቶ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑ አጋማሹን በአስተማማኝ መሪነት እንዲያገባድድ አድርጓል።

የፋሲል ከነማ መሸነፉን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡት ባህር ዳር ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከባዱን ፈተና ለመጋፈጥ እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ይህ ቢሆንም ግን አለልኝ አዘነ በ58ኛው ደቂቃ ከሞከረው የሰላ ጥቃት ውጪ ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ጨዋታው ቀጥሏል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ያገኙትን የሰፋ የጎል ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወት ይዘዋል።

የባህር ዳር ግብ ለማስቆጠር ነቅሎ መውጣት የቀጠቀማቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ምስጋነው መላኩ ሙከራ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። እንደ አጀማመሩ በጥሩ ፉክክር ያልዘለቀው ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። የምዱቡ ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ9 ነጥቦች አንደኛ ሆኖ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲያልፍ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በአራት ነጥብ ተከታይ ሆኖ አልፏል።

ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ፀጋዬ መላኩ ደግሞ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ 12 ሺ ብር እና የዋንጫ ሽልማቱን ተቀብሏል።