አራት የሀገራችን ዳኞች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለመምራት ዛሬ ምሽት ወደ ቱኒዚያ ያመራሉ

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚደረጉ የአህጉራችን ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ፍልሚያ ለመዳኘት አራት የሀገራችን ዳኖች ዛሬ ምሽት ወደ ቱኒዚያ ያመራሉ።

ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች በምድብ ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። በምድብ ሁለት የተደለደሉት ቱኒዚያ እና ሞሪታኒያ ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ቱኒዝ ላይ ያደርጋሉ። ይህንን ጨዋታ ደግሞ በዓምላክ ተሰማ በመሐል ዳኝነት እንደሚመራው ታውቋል።

የባምላክ ረዳቶች ሆነው በመስመር ዳኝነት ደግሞ ተመስገን ሳሙኤል እና ፋሲካ የኋላሸት መመደባቸው ተጠቁሟል። ሌላኛው የሀገራችን ዳኛ በላይ ታደሠ በበኩሉ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ እንደሆነ ተመላክቷል። አራቱም ዳኞች ዛሬ ምሽት ወደ ስፍራው በማምራት በምድቡ አናት እና ግርጌ የሚገኙትን የቱኒዚያ እና ሞሪታኒያ ጨዋታ የሚመሩ ይሆናል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፀሐፊ አቶ ሠለሞን ገብረስላሴ ደግሞ ከነገ በስትያ ሞሮኮ ላይ የሚደረገውን የሱዳን እና ጊኒን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በኮሚሽነርነት ለመምራት ወደ ስፍራው እንዳቀኑ ሰምተናል።