ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | ሀዲያ ሆሳዕና ድል ሲቀናው ሰበታ ከተማ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የአራተኛ ዙር ሁለተኛ ጨዋታ ከሰዓት ቀጥሎ ሀዲያ ሆሳዕና በሀብታሙ ታደሰ ብቸኛ ጎል ሀዋሳ ከተማን ማሸነፉን ተከትሎ ሰበታ ከተማ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

9፡00 ሲል የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ተደርጓል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ መሀል ሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን አጥረው የዋሉበት እና መጠነኛ ኃይል የቀላቀለ የአጨዋወት መንገድ ያስተዋልንበት ሆኗል፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ በፈጣን የቅብብል ሂደት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ሀዲያ ሆሳዕና የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም መድሀኔ ብርሀኔ በግራ በኩል ማስቆጠር የሚችልበትን ነፃ ዕድል 6ኛው ደቂቃ ላይ አምክኗል፡፡ ጥቂት በቁጥር የሚጠቀሱ ሙከራዎችን ብቻ ለማየት በተገደድንበት በዚህ አጋማሽ ቡድኖቹ ለመጫወት የፈለጉት የጨዋታ መንገድ ግቦችን ከማግኘት አንፃር አዋጭ ሲሆንላቸው አልታየም፡፡

በ10ኛው ደቂቃ ከቀኝ በኩል በረጅሙ የተሻማን ኳስ የሀዲያው ፀጋዬ ብርሀኑ በግንባር ገጭቶ በግቡ የላይኛው ብረት የወጣችበት እና 20ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከሳምሶን ጥላሁን ያገኛትን በግንባር ገጭቶ የሳታት የነብሮቹ ሁለት ጠንካራ ሙከራዎች ናቸው፡፡ 30ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማ እጅግ አስቆጪ አጋጣሚን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ አማካዩ ወንድማገኝ ኃይሉ የግል አቅሙን በመጠቀም ለአጥቂው ብሩክ በየነ አቀብሎት ብሩክ በፍጥነት ያገኘውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ ቢመታም መሳይ አያኖ ይዞበታል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ጉልበት አዘል ሆኖ ቀጥሏል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ሀዲያ ሆሳዕና መሪ የምታደርግ ዕድልን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም መጠቀም አልቻለም። ከግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመስመር ተጫዋቹ በግብ ጠባቂው የተመለሰበት ጠንካራዋ ሙከራ ነበረች፡፡ ጨዋታው ጉልበት አዘል መሆኑን ተከትሎ 52ኛው ደቂቃ ላይ ቀይ ካርድ ተመልክተናል። ኤፍሬም አሻሞ የሀዲያ ሆሳዕናው ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ጥፋት ሰርቶብኛል በቀይ መውጣት አለበት ብሎ ተጫዋቹም ሆነ የሀዋሳ የቡድን አባላት በጠየቁበት ቅፅበት ህክምና ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የተመለሰው ኤፍሬም አሻሞ ከመስመር ላይ ኳስን ጀምሮ ኳሱን ለመንጠቅ የተጠጋው አስቻለው ግርማ ላይ አደገኛ ጥፋት በመስራቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ለማጣት የተገደዱት ሀዋሳዎች እየተቀዛቀዙ ሲመጡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ይበልጥ ግቦችን ለማግኘት በተለይ በመስመር ባጋደለ የማጥቃት ሂደት ተንቀሳቅሰዋል፡፡በዚህም 76ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ለማጥቃት ነቅለው በወጡበት ወቅት ኳስ መሀል ሜዳ ላይ በመቋረጡ የተነሳ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በቀኝ መስመር ጥቃት በመክፈት ፀጋዬ ብርሀኑ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ሀብታሙ ታደሰ ሰጥቶት የመስመር ተጫዋቹም ወደ ጎልነት ቀይሮ ሀዲያ ሆሳዕናን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቡ መገኘት በኋላ በድጋሚ ፀጋዬ ብርሀኑ ግልፅ የማግባት ዕድልን አግኝቶ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ መልሶበታል፡፡

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የሀዲያ ሆሳዕና የተከላካይ መስመር ማለፍ ቢሳናቸውም በተወሰነ መልኩ ሀዋሳዎች በብሩክ በየነ እና ተቀይሮ በገባው ብሩክ ኤልያስ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚያስችላቸውን ዕድሎች ከአንድም ሁለት ጊዜ ፈጥረዋል፡፡በተለይ ብሩክ ኤልያስ ወደ ሳጥን በድፍረት ነድቶ ገብቶ ለሌላኛው ብሩክ ሲያቀብለው ከግቡ ትይዩ የነበረው ተጫዋቹ በቀላሉ አምክኗታል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በጭማሪ ደቂቃዎች ሀዲያዎች በሀብታሙ ታደሰ ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ደስታ ዋሚሾ አማካኝነት የሚያስቆጩ ተጨማሪ የግብ ማስቆጠር ዕድሎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከመረብ ማሳረፍ ሳይችሉ ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡ ሀዋሳ መሸነፉን ተከትሎም ረፋድ ላይ ድሬዳዋን የረታው ሰበታ ከተማ የመጀመሪያው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዲያ ሆሳዕናው የመሀል ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ የጨዋታው ምርጥ ተብሎ ተሸልሟል፡፡