የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ እና አምበል ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

👉”በመጀመሪያው ጨዋታ አሸንፈን መምጣታችን ምንም ወደ ኋላ አይጎትተንም” ፍሬው ኃይለገብርኤል

👉”ቡድናችን ላይ ያለው ነገር በጣም ደስ ይላል” ናርዶስ ጌትነት

በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የዓለም የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ የሚያሳትፋቸውን ትኬት ለማግኘት የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በቀጥታ ሁለተኛውን ዙር ማጣሪያ ተቀላቅሎ ከሩዋንዳ ጋር ተደልድሏል። ብሔራዊ ቡድኑም የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሳምንት በፊት ወደ ኪጋሊ አቅንቶ ያደረገ ሲሆን አስተማማኝ የሚመስለውን የአራት ለዜሮ ውጤት ይዞ ተመልሷል። ቡድኑም በነገው ዕለት የመልስ ጨዋታውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚያከናውን ሲሆን አሠልጣኙ እና አምበሏም ከጨዋታው በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሶከር ኢትዮጵያን እና ትዕንግርት የሴቶች ስፖርት ብቻ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም በቅድሚያ አሠልጣኝ ፍሬው ለጨዋታዎቹ ያደረጉትን አጠቃላይ ዝግጅት እና የመጀመሪያውን ጨዋታ የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ሩዋንዳ ከመሄዳችን በፊት የ22 ቀናት የዝግጅት ጊዜ ብቻ ነበረን። ባለን ጊዜ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ መፍትሄ ለማምጣት ስንጥር ነበር። ባለን ውስን ጊዜ ልምምድ ከመስራት በተጨማሪም ከቢሾፍቱ ቢ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገን ነበር። ከጊዜ መጣበብ ጋር ተያይዞ ቅርፁን የጠበቀ ቡድን ሙሉ ለሙሉ ለመገንባት አልቻልንም። ባለን ነገር ግን ለመስራት ጥረናል። በመጀመሪያ ከጠራናቸው 40 ተጫዋቾች በጉዳት እና በውድድር ምክንያት (የባንክ) እንዲሁም በግል ጉዳይ ያልነበሩ ተጫዋቾች ነበሩ። የሆነው ሆኖ ጥሩ ነገር ሰርተን ወደ ሩዋንዳ 20 ተጫዋቾችን ይዘን ሄደናል።

“ሩዋንዳ ላይ የተጫዋቾቼ የማሸነፍ ስሜት የሚገርም ነበር። የቡድኑ አምበል ዮርዳኖስ ጌትነት ከእኔ ጎን ለጎን ቡድኑን ሜዳ ላይ ስትመራ ነበር። ተጫዋቾቼ የሚባሉትን ነገር በደንብ ይሰማሉ። ለዛም ነው በ22 ቀን ተዘጋጅተን ጨዋታውን ያሸነፍነው። ውጤታማ የሆንነውም እንደ ቤተሰብ ስለምንተያይ ነው። ጨዋታው ላይ አራት ለባዶ አሸንፈናል። ግን ክፍተቶች አልነበሩብንም ማለት አይደለም።” ብለዋል።

አሠልጣኙ ቀጥለው ስብስባቸው ከሩዋንዳ ከመጣ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት ማብራራት ይዘዋል። “ከሩዋንዳ እንደመጣን 2 ቀን ለተጫዋቾቹ እረፍት ሰጥተናቸው ነበር። ከዛም ከመስቀል በዓል በኋላ ሁለት ቀን የጂም ስራዎችን ሰርተናል። ከዛም አዲስ አበባ የመስክ ስራ ሰርተን ወደ ባህር ዳር መጥተናል።” ካለ በኋላ “ለነገውም ጨዋታ ያለን ዝግጅት ከፍተኛ ነው። የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱም ሆነ ተጫዋቾቹ በጥሩ ሥነ-ልቦና ላይ ይገኛሉ። ሩዋንዳ አሸንፈን መምጣታችን ምንም ወደ ኋላ አይጎትተንም። ተመሪ መሪውን ነው የሚመስለው። እኛም ምንም እንዳይዘናጉ ነግረናቸዋል።”

በተከታይ በመጀመሪያው ጨዋታ የነበረው የግብ ልዩነት መስፋት ከምን የመጣ ነው ተብለው የተጠየቁት አሠልጣኙ “በእግርኳስ ሁሉም ቡድን ለመሸነፍ አይዘጋጅም። ሩዋንዳዎች ከእኛ የተሻለ ጊዜ አግኝተው ሲዘጋጁ ነበር። እኛ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ቪዲዮዋችንም አላገኘንም። በጨዋታው እነሱም ለማሸነፍ ነበር የመጡት። እኛ ግን ጥሩ ሆነን ቀርበን ስለነበር ጨዋታውን አሸንፈናል። በጨዋታው አራት ግቦችን ብናገባም የተሻሉ የግብ ማግባት እድሎችን ፈጥረን ነበር። ግን የበለጠ ማስቆጠር አልቻልንም። በመከላከሉም ረገድ ጠንካራ ነበርን። እስከ 25ኛው ደቂቃ ድረስ ግን ሩዋንዳዎች በጣም ሲከላከሉ ነበር። በስህተት ባስቆጠርናቸው ጎል ግን በደንብ አስከፍተናቸው ተጨማሪ ጎሎችን አስቆጥረን ወጥተናል።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

የመጀመሪያው ውጤት በነገው ጨዋታ ላይ መዘናጋት አያመጣም ወይ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ “ጨዋታውን ጨርሰናል ብለን ተከላክለን አንወጣም። ነገ በጣም የሚያጠቃ እና በእውቀት የሚጫወት ቡድን ሜዳ ላይ ለማሳየት እንሞክራለን። የማሸነፍ ሥነ-ልቦናችን እንዲቀጥል በክፍል ውስጥ ተጫዋቾቹን በደንብ አስተምረናል። በጨዋታውም መዘናጋት ይኖራል ብዬ አላስብም።”

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ጨዋታ መመለሳቸው በመጀመሪያው ጨዋታ የተወሰነ ተፅእኖ እንዳመጣ በንግግራቸው የጠቆሙት አሠልጣኝ ፍሬው ችግሩን ለመቅረፍ በነበራቸው ውስን ጊዜ መፍትሔዎችን ለማምጣት እንደሞከሩ አመላክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም አብዛኞቹ ተጫዋቾች የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የሌላቸው መሆኑም በጨዋታው ላይ መጠነኛ ክፍተት ቢያመጣም በተቻለ መጠን በመነጋገር ችግሩ እየተቀረፈ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከቡድኑ ዜና ጋር በተገናኘ ተከላካዩዋ ብዙዓየሁ ታደሠ በሀዘን ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ከቡድኑ ጋር እንደማትገኝ ሲገለፅ በዚህም ምክንያት ቡድኑ እንደተከፋ እና የእሷ አለመኖር ተፅእኖ እንደሚፈጥር አሠልጣኝ ፍረው አውስተዋል። ይህ ቢሆንም ግን የእሷን ቦታ ሸፍነው መጫወት የሚችሉ ወጣት ተጫዋቾች ነገ እድል እንደሚያገኙም ተጠቁሟል። ከእሷ ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

በመጨረሻ በመግለጫው ቡድን የመምራት የተሻለ አቅም እንዳላት በዋና አሠልጣኙ ሲነገር የተደመጠው አምበሏ ናርዶስ ጌትነት በአጭሩ የቡድኑን መንፈስ በተመለከተ ተከታዩን ብላለች።

“ቡድናችን ላይ ያለው ነገር በጣም ደስ ይላል። ተመሳሳይ እድሜ ላይ ስላለን ነው መሰለኝ ጥሩ መናበብ አለን። አሠልጣኛችንም በዚህ ላይ በጣም ሰርቷል። በአጠቃላይ ተጫዋቾቹ ጋር ጥሩ የአንድነት መንፈስ አለ። የነገውንም ጨዋታ በጉጉት እየጠበቅነው ነው።”