“እኛ ራሳችንን በሩዋንዳ ልክ አናስቀምጥም ፤ ወደ ላይም አናደርግም” ፍሬው ኃይለገብርኤል

በዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የሩዋንዳ አቻውን በድምር ውጤት 8-0 ያሸነፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የሚመሩት አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከዛሬው ጨዋታ በኋላ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

በጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው?

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር መጓጓት ነበር። ባለፈውም የነበረብን ስህተት ያ ነው አሁንም ሲደገም አይቼዋለው። ሁሉም ነገር በሥራ ነው የሚለወጠው። ስለዚህ ጎል ለማግባት እንጂ ቡድኔ የተቸገረው ብዙም ብልጫ ተወስዶበት አይደለም። ብልጫ እንወስዳለን ግን ከጉጉት የተነሳ አጋጣሚዎችን እናመክናለን። በተቀረ ጎሉ በገባ ቁጥር እየተስተካከለ እየተስተካከለ ሲመጣ ቡድኑን አይተነዋል። ወጣቶች ናቸው ብዙ መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ። ከ20 ዓመት በታች ቡድን እንደመሆኑ መጠን ነገሮችን እያስተካከልን እንሄዳለን። ይህ ቡድን በዚህ ብቻ የሚቀር አይደለም። አዳዲስ ፊቶችን እያመጣን ማስተካከያዎችን እየወሰድን እንሄዳለን። ስለዚህ የዛሬው ጨዋታ ትንሽ ጭንቀት ውስጥ ከመግባት እንጂ ብዙም ብልጫ ተወስዶባቸው አይደለም።

ጭንቀቱ ከምን የመጣ ነው ?

ተጫዋቾቹ ከፍ ያለ የማሸነፍ ፍላጎት ስላላቸው ነው። ይህ ነው እንጂ ሌላ ምንም ነገር የለም።

የተጋጣሚ አቋም ቡድኑን በሚገባ ለማየት የሚያስችል ነበር ?

የሚመጡ ቡድኖች አይፈትኑንም አይባልም። ሁሉም ሊፈትን ሊበልጥ ነው የሚመጣው። ስለዚህ እኛ ራሳችንን በሩዋንዳ ልክ አናስቀምጥም ፤ ወደ ላይም አናደርግም። ሁል ቀን ለአዲስ ሥራ የሚያዘጋጅ አዕምሮ ይኖረናል እኔም ሆንኩ ተጫዋቾቼ። ለሚመጣው ቡድን ሁሉ እያስተካከልን ነው የምንሄደው። አሁን ባለን ጨርሰናልም ይቀረናልም ማለት አይቻልም በእግርኳስ። ይህ ጨዋታ ሁሉም ሊያሸንፍ ነው የሚመጣው። ሁሉም ቡድን ይፈትናል 25-30 ደቂቃ እየፈተኑን ነበር። አስቀጥሎ ውጤት ይዞ መውጣቱ ላይ ነው ልዩነቱ። በዛ ደግሞ ልዩነት ፈጣሪዎች ሆነን ወጥተናል።

ከመጀመሪያው ጨዋታ አንፃር ቡድኑ ላይ የታየ ዕድገት ስለመኖሩ…?

ተጫዋቾቹ ታዳጊዎች ናቸው። ባለፈው ሦስት አሁን ደግሞ አምስት ተጫዋቾች ለውጠን አይተናል። አንደኛው ለውጥ ይህ ነው። በዛ ያሉ ተጫዋቾችን ሜዳ ላይ ማየት ችለናል። ከተጠሩት ውስጥ ከግብ ጠባቂዎቹ በቀር ሌሎቹን እንዳይ አድርጎኛል። ከዛ በተጨማሪ ኳስ በመያዙ ረገድ ቡድናችን ላይ የተሻለ ነገር እያየን ነው። ቅርፅ ያለው ቡድን መሰራት ካለበት በመጀመሪያ ኳስ መያዝ ላይ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ። ቀጥተኛ ወይስ ቀጥተኛ ያልሆነ ኳስ ነው የሚያዋጣን ለሚለው እንደሀገር ታስቦ በሚጠቅመን መንገድ ለመሄድ ተጫዋቾቹ ላይ ምን ይሰራ የሚለውን ወደፊት እያስተካከልን እንሄዳለን።

በአጠቃላይ ለማጣሪያው የነበራቸሁ ቆይታ ምን ይመስላል?

ከወትሮው በተለየ ተጫዋቾቹ ጥሩ ነገር እያደረገላቸው ነው የሚገኘው። ከፕሬዘዳንት እና ከፀሀፊ ጀምሮ ልምምድ ሜዳ ላይ በመገኘት ቡድኑን በማበረታታቸው እና ሁሉንም በዕኩል አይን በማየታቸው እግርኳስ ፌዴሬሽኑን ማመስገን እፈልጋለሁ። ሥራ አስፈፃሚው በተሰጣቸው የስራ መደብ ላይ ጥሩ ማበረታቻ ሲያደርጉልን ነበር። ተጫዋቾቼም በዚህ ደስተኛ ናቸው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ብዙ የተቸገርኩበት ነገር የለም። በቁሳቁስም ሀገራዊ ነገሮች እየተደረገልን ስለሆነ እጅግ በጣም ደስ ይላል። ሴቶች ክብር አላቸው አክብረው እያደረጉላቸው ስለሆነም በድጋሚ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ለቀጣዩ ጨዋታ በአዲስ መልክ እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ። ቡድኑ መሄድ እስካለበት ድረስ እንደምናስኬደው ደግሞ በጣም እርግጠኛ ነኝ።