ንግድ ባንክ ሁለት አዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአንድ ነባር ተጫዋቹንም ውል አድሷል

ከሰዓታት በፊት የወሳኟን አጥቂ ሎዛ አበራን ውል ያደሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአማካዩን ውል ሲያድስ ሁለት አዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ዋንጫ ዓምና ከፍ ማድረጉ ይታወሳል። በአዲሱ የዘንድሮ ዓመትም ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ያሰበ የሚመስለው ክለቡ ከሦስት ወራት በፊት የስድስት ተጫዋቾችን ዝውውር ማገባደዱ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ዳግም በገበያው በመሳተፍ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

ክለቡን የተቀላቀለችው የመጀመሪያዋ ተጫዋች እፀገነት ብዙነህ ነች። የቀድሞ የደደቢት እና አዳማ ከተማ ተጫዋች የነበረችው እፀገነት ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫዎችን በማንሳት ባለ ታሪክ ተጫዋች እንደሆነች ይታወቃል። አሁን ደግሞ ለስድስት ዓመታት የተጫወተችበትን ክለብ ዳግም ከአራት ዓመታት በኋላ በመቀላቀል በዛሬው ዕለት የሁለት ዓመት ውል ፈርማለች።

ከእፀገነት በተጨማሪም ታዳጊዋን ተጫዋች ትዕግስት ጌታቸው ለንግድ ባንክ የሁለት ዓመት ፊርማ አኑራለች። በኦሮሚያ ክልል ቅምብቢት ወረዳ ከወንዶች ጋር እግርኳስ ስትጫወት ያዩዋት የክለቡ አሠልጣኝ ብርሃኑም በአጥቂዋ ተማምነው ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋታል።

ክለቡ የሁለቱን ተጫዋቾች ዝውውር ባጠናቀቀበት ዕለት ያለፉትን ሦስት ዓመታት የተጫወተችውን አማካይ ብርቱካን ገብረክርስቶስንም ውል ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።