የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ

ሌላኛው ከከፍተኛ ሊግ የተመለሰውን የአርባምንጭ ከተማን መጪው የውድድር ዓመት በዚህ መልኩ ቃኝተነዋል።

2004 ላይ ፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅሎ የቆየው አርባምንጭ ከተማ 2010 ላይ ነበር ሊጉን የተሰናበተው። በኮቪድ ወረሺኝ ምክንያት የተሰረዘውን ዓመት ሳይጨምር በሁለተኛው የሊግ ዕርከን ሁለት ዓመታትን አሳልፎ በዘንድሮው ውድድር ምልሰቱን ያደርጋል። ዐምና በተካፈለበት የከፍተኛ ሊግ የክለቡ አካሄድ በትክክልም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ የነበረውን ቁርጠኝነት ያመለክታል። በተመደበበት ምድብ ሐ ላይ 22 ጨዋታዎችን ሲያደርግ ውድድሩን ያለሽንፈት ነበር ያጠናቀቀው። ማግኘት ከነበረበት 66 ነጥቦች 52ቱን ማሳካቱም አስገራሚ ዓመት ለማሳለፉ ዋና ማስረጃ ነው። ይህንን የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማሻገር ደግሞ የአርባምንጭ ከተማ ቀጣይ ፈተና ይሆናል።

አርባምንጭ በከፍተኛ ሊግ ባሳለፈባቸው ዓመታት በዋና አሰልጣኝነት የመሩት እና ወደነበረበት እንዱመለስ የረዱት የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ውል በአንድ ዓመት በማራዘም የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅቱን ጀምሯል። በመቀጠልም 2010 ላይ የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ማቲዮስ ለማን ዳግም ሲሾም ነባር የነበሩት አሰልጣኝ አበው ታምሩ እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ስለሽ ሽፈራው ውልም ታድሷል። ማቱሳላ ሶራቶ እና መንግሥቱ ደምሴ ደግሞ በህክምና ባለሙያነት እና በቡድን መሪነት አርባምንጭን የሚያገለግሉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ፉክክር ከታች አድገው የሚቀላቀሉ ክለቦች ስብስባቸውን እንደአዲስ ሲከልሱ እና በሊጉ ክለቦች የቆዩ ተጫዋቾችን በብዛት ሲያሰባስቡ ይታያል። በዘንድሮዎቹ አዳጊዎች አዲስ አበባ እና መከላከያም የስብስብ ለውጦች በርከት ብለው ተመልክተናል። ወደ አርባምንጭ ከተማ ስንመጣ ግን ከዚህ ቀደም በርካታ እግርኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት ይታወቅበት የነበረበትን መንገድ ማስቀጠልን ምርጫው ያደረገ ይመስላል። ይህ በመሆኑም አካባቢው ያፈራቸው ተጫዋቾች ላይ ዕምነቱን በመጣል እስካሁን የመጣበትን አመዛኙን ስብስቡን ኮንትራት በማራዘም ማቆየትን መርጧል። በዚህም መሰረት ናይጄሪያዊውን ተከላካይ ማርቲን ኦቼናን ጨምሮ 12 የሚደርሱ ክለቡን በከፍተኛ ሊግ ያገለገሉ ተጫዋቾች ለፕሪምየር ሊጉም ፍልሚያ ብቁ እንደሆኑ በማመን ውላቸው እንዲታደስ አድርጓል።

ክለቡ ራሱን ለማጠናከር ተጨማሪ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም በክረምቱ በሀገራችን አስተናጋጅነት የተደረገው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ውድድርን አንደኛው የመመልመያ አማራጩ አድርጓል። በውድድሩ ከተካፈሉ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ሁለት ኬኒያዊያንን በስብስቡ አካቷል። በርናንድ ኢቼንግ እና ኤሪክ ካፖቶይ የተባሉት ኬኒያዊያን የተከላካይ እና የአማካይ መስመር ተጫዋቾች ናቸው የአሰልጣኝ መሳይን ቀልብ ስበው የአዞዎቹ አካል የሆኑት። የተቀሩትን ቦታዎች ዓመቱን በከፍተኛ ሊግ ባሳለፉ ተጫዋቾች በመሙላት የቀጠለው አርባምንጭ አንጋፋውን ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋን አስፈርሟል። የፕሪምየር ሊግ ልምድ ቢኖረውም በ2013 በአዲስ አበባ ከተማ ከነበረው ግብ ጠባቂ በተጨማሪ በዛው ዓመት ለመከላከያ ሲጫወት የቆየው ሱራፌል ዳንኤልን ጨምሮ እንዳልካቸው መስፍን እና አቡበከር ሻሚልን አማካይ ክፍል ላይ ሀቢብ ከማል እና አሸናፊ ተገኝን በአጥቂ ስፍራ ላይ ወደ ስብስቡ አምጥቷል።

አሰልጣኝ መስይ ተፈሪ እንደ ቀደመ ክለባቸው ወላይታ ድቻ ሁሉ ወደ ሊጉ ያመጡት አርባምንጭ ከተማ ያለፉት ሁለት የውድድር ዓመት ጉዞ በቡድኑ ላይ እንዲተማመኑ አድርጓቸዋል። በስብስባቸው ላይ በርካታ ለውጦችን ያለማድረጋቸውን መነሻ ሲያስረዱም “አብዛኞቹን ተጫዋቾች አቆይተናል። በሁለት ዓመት ጥቂት ጨዋታዎችን የተሸነፈ ጠንካራ ቡድን ነው። ይህንን ተከትሎም ቡድኑን የመነካካት ፍላጎት አልነበረንም። ግን የማጠናከር ሥራ ከፕሪምየር ሊጉም ሆነ ከተለያዩ አካባቢዎች በማምጣት ሰርተናል። በተለይ በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸውን እንደነ ሳምሶን እና ሱራፌል ዓይነት ተጫዋቾችን አምጥተናል። ከዚህ ውጪ ከእኛ አጨዋወት ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ተጫዋቾችን አስፈርመናል። በአጠቃላይ በዝውውሩ የነበረን ወጪ ያን ያህል የተጋነነ አይደለም። ከዚህ ውጪ ባህር ዳር ላይ በተከናወነው የሴካፋ ውድድር ጠንካራ የነበሩ ተጫዋቾችን አምጥተናል።” በማለት ነበር።

“ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ተስፋ ያላቸውን ተጫዋቾች እናያለን።” የሚሉት አሰልጣኙ 25 ተጫዋቾችን ከያዘው ስብስብ በተጨማሪ ግብ ጠባቂው ሰራዊት ኪያ ፣ ተከላካዮቹ መልካሙ በርገኔ እና በረከት ሳሙኤልን አጥቂው ዮርዳኖስ ኢያሱ እንዲሁም አማካዮቹ ቤዛ አበበ እና አቤንዘር ሳሙኤልን ከዕድሜ እርከን ቡድኖቹ አሳድጓል። ከእነዚህ ወጣቶች በተጨማሪም ሌሎች አራት ተጫዋቾች በልዩ ቴሴራ መካተት ችለዋል።

በፕሪምየር ሊጉ ከወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጋር ልምድ ያላቸው የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የዘንድሮው ቡድን ወረቀት ላይ ከተፎካካሪዎቹ ጋር ሲተያይ የቅርብ ጊዜ የሊግ ልምድ ያንሰዋል። ይህ መሆኑ ብቻውን የአርባምንጭን ውጤት ዝቅ ያደርጋዋል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በሀገራችን ያለው የተጫዋቾች ጥራት ደረጃ የተጋነነ እንዳልሆነ አጥብቀው ለሚያምኑ የስፖርቱ አፍቃሪያን ግን የዘንድሮው የአርባምንጭ ጉዞ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ነው። በሌላ ጎኑ ስንመለከተው በሁለተኛው የሊግ እርከን ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ራሳቸውን ከፍ ባለው መድረክ የማስመስከር ርሀባቸው ቡድኑን ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። ተጫዋቾቹ በነባሩ ክለባቸው መሆኑ ፕሪምየር ሊጉን የሚቀላቀሉት ደግሞ የእኔነት ስሜታቸውን የሚያጠናክር ነው ማለት ይቻላል።

አርባምንጭ ከተማ በዚህ አኳኋን የተገነባው ስብስቡን ይዞ ከነሐሴ 15 ጀምሮ በመቀመጫ ከተማው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል። እንደ አሰልጣኙ ገለፃም ቡድኑ በአካል ብቃት፣ በታክቲክ እና በቴክንኒኩ ላይ ይበልጥ ትኩረቱን አድርጎ ሲዘጋጅ ከርሟል። የቡድኑ አብዛኛው ክፍል ባልተበተኑ ተጫዋቾች መዋቀሩ የውህደት ሥራዎችን ለአዞዎቹ ቀለል እንደሚያደርጋላቸው እሙን ነው። “አዲሶቹን ከነባሮቹ ጋር የማዋሐድ ስራው ጥሩ ነው የሄደልን። የመጡት ተጫዋቾችም ያለውን ነገር የመቀበል እና የመግባባት አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ይህንን ተከትሎ በጥሩ ሁኔታ ነው ዝግጅታችንን እያደረግን ያለነው።” የሚለው የአሰልጣኝ መሳይ አስተያየትም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው።

አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮ አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ላይ በተደረጉ የዝግጅት ውድድሮች ላይ አልተካፈለም። ይህም በተመሳሳይ ሁኔታዎች ካለፉት ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጋር ያመሳስለዋል። ሁለቱ ቡድኖች አምና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ ያደረጉ መሆናቸውን ስናይ ግን የአርባምንጭን የተለየ ያደርገዋል። የስብስቡ በአመዛኙ ነባር መሆን አንድ ነገር ሆኖ ሳለ በፉክክር ጨዋታዎች ውስጥ ቢያልፍ ይበልጥ የተሻለ ይሆን እንደነበር ግን ዕሙን ነው። አሰልጣኙም ጨዋታዎችን የማድረግ ጥቅሙን ቢያምኑም ሳይሆንላቸው መቅረቱ ግን ብዙ ምቾት የነሳቸው አይመስሉም። ” ጨዋታዎችን ማድረጉ ጥቅም አለው። እኛ ጨዋታዎችን ለማድረግ ሞክረናል። ግን ያሰብነውን ያህል አልተጫወትንም። ትልቁ ነገር አብሮነቱ ቡድናችን ውስጥ አለ። ከወልቂጤ እንዲሁም ከተስፋ ቡድን ጋር እና ከከፍተኛ ሊግ እና ፕሪምየር ሊግ ከተወጣጡ ተጫዋቾች ያዋቀሩት ቡድን ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቻችንን አይተናል። ግን የሄድንበት መንገድ አዋጪ ነው የሚለውን በቀጣይ ውድድሮች ላይ ነው የምናየው።” በማለትም ስለሁኔታው ያብራራሉ።

ከአጨዋወት መንገድ ምርጫ አንፃር አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ወላይታ ድቻን ወደ ሊጉ ሲያሳድጉ ይከተሉት የነበረውን የጨዋታ መንገድ በአርባምንጭ ከተማም እንደሚያያስመለክቱን ይጠበቃል። በዚህም ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ያለው ለተጋጣሚዎቹ ክፍተት ላለመስጠት እንደቡድን የሚከላከል ክፍተቶች ሲፈጠሩ በቶሎ ወደግብ ለመድረስ የሚሞክር አርባምንጭ በሊጉ ይጠበቃል። ቡድኑ አምና በከፍተኛ ሊጉ በ 22 ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት መሆኑ በዚህ የነበረውን ጠንካራ አቋም ያስረዳናል። በዝውውር ጊዜው የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ኮታውን ሲሞላ ካስፈረመው ኬኒያዊው በርናንድ ኢቼንግን ውጪ ሌላ የኋላ መስመር ተጫዋች ለማግኘት አለመንቀሳቀሱ ደግሞ አሰልጣኙ እንደ አጠቃላይ ቡድኑ ሁሉ የተከላካይ ክፍል መሰረታቸውን እምብዛም መንካት እንዳልፈለጉ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ከኋላ እስካሁን የመጣበትን ውህደት በመጠቀም እና በቀሩት የቡድኑ ክፍሎች ጥሩ ሽፋን በመስጠት ከግብ ክልሉ ሳይርቅ የመንቀሳቀስ ዕቅድ እንዳለው መገመት ይቻላል።

ይህንን ለማስፈፀምም በአካል ብቃት ደረጃው ሙሉ ጨዋታን ከስህተት ርቆ በጀመረበት ትኩረት የሚፈፅም ቡድን ከአሰልጣኝ መሳይ ይጠበቃል። በማጥቃቱ ረገድ ቀጥተኛነትን መሰረት ያደረገ አቀራረብ ሊኖረው እንደሚችል የሚጠበቀው አርባምንጭ ከኋላ እና ከአማካይ ክፍሉ መካከለኛ እና ረዘም ያለ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ ተጋጣሚ ሳይደራጅ ሳጥን ውስጥ የመግባት ሀሳብን ይየሚተገብር ይሆናል። በዚህ ረገድ የፊት መስመሩ በፍጥነት ሦስተኛው የሜዳው ክፍል ላይ የመድረስ እና ጥሩ የአጨራረስ ንፃሬን ማስመዝገብ አስፈላጊው ይሆናል።

ልምድን ከማካፈል እና ወጣቶችን ከመምራት አንፃር በስብስቡ ውስጥ ያሉት ሳምሶን አሰፋ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ሱራፌል ዳንኤል ዓይነት ተጫዋቾች በሌላ ማልያም ቢሆን የቅርብ ዓመታት የሊግ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ከፍ ያለ አበርክቶት ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም አምና በሁለተኛው ዙር ጥሩ የተንቀሳቀሰው ራምኬል ሎክ ራሱን በድጋሚ በፕሪምየር ሊጉ በጥሩ ብቃት የማሳየት ዕድል ከፊቱ ይጠብቀዋል። ሌላኛው አጥቂ አሸናፊ ተገኝም ለአርባምንጭ ጥሩ ግልጋሎትን ሊሰጥ ይችላል። የቀደመ ክለቡን ዳግም የተቀላቀለው አሸናፊ በጋሞ ጨንቻ ያሳየውን የግብ አስቆጣሪነት ብቃት በሊጉ መድገም ከቻለ የእግርኳስ ህይወቱ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ሊሻገር ይችላል።

1995 ላይ ድንቅ ቡድን ገንብቶ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቦ ከነበረው አርባምንጭ ጨርቃጨርቅ በኋላ የከተማዋ ክለብ በውጤት ደረጃ የተለየ ታሪክ አላስመዘገበም። ዘንድሮው ከከፍተኛ ሊጉ ዳግም ሲመለስ የፉክክር ደረጃው እስከምን ይሄዳል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ መሆኑም አያጠያያቅም። ለወትሮው ከታች የሚመጡ ቡድኖች ዋነኛ ዓላማ ለከርሞው በሊጉ መቆየትን ማረጋገጥ ሲሆን ቢታይም አሰልጣኝ መሳይ ግን ከዚያ ያለፈ ሀሳብ አላቸው። “ቡድናችን ጥራት ያለው እና ጥልቀት ያለው ነው። አርባምንጭ ቀድሞ የነበረውን ታሪክ ለመድገም የሚያስችል ቡድን ነው ውድድሩ ላይ ይዘን የምንቀርበው። እኛ ጠንካራ ነገር አለን። የምናደርጋቸውንም እያንዳንዱን ጨዋታዎች በድል ለመወጣት ነው የምንጥረው።” በማለት ተፎካካሪ የሆነ አርባምንጭን እንድንጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአርባምንጭ ከተማ የ2014 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 ሳምሶን አሰፋ
30 ይስሐቅ ተገኝ
31 መኮንን መርዶክዮስ
ሰራዊት ኪያ (U-23)


ተከላካዮች

2 ተካልኝ ደጀኔ
3 መላኩ ኤሊያስ
4 አሸናፊ ፊዳ
5 አንድነት አዳኔ
6 ደረጄ ፍሬው
12 ሙና በቀለ
14 ወርቅይታደስ አበበ
15 በናርድ ኦችንጌ ኦጊንጋ
25 ኡቸና ማርቲን ኦክሮ
መልካሙ በርገኔ (U-23)
በረከት ሳሙኤል (U-23)


አማካዮች

8 አብነት ተሾመ
17 አሸናፊ ኤሊያስ
18 አቡበከር ሻሚል
20 እንዳልካቸው መስፍን
21 አንዱአለም አስናቄ
22 ፀጋዬ አበራ
27 ሱራፌል ዳንኤል
ቤዛ አበበ (U-23)
አቤንዘር ሳሙኤል (U-23)

አጥቂዎች

7 አሸናፊ ተገኝ
9 በላይ ገዛኸኝ
10 ራንኬል ሎክ
11 ፍቃዱ መኮንን
23 ሀቢብ ከማል
26 ኤሪክ ካፓይቶ ሙጊ
ዮርዳኖስ ኢያሱ (U-23)


ተጨማሪ የምስል ግብዓት፡ Arba Minch City F.C/ አርባ ምንጭ ከነማ – The Crocodiles