ሪፖርት | ባህር ዳር ሊጉን በሰፊ ድል ጀምሯል

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 3-0 ማሸነፍ ችሏል።

ቀዳሚው አጋማሽ በቁጥር በበዙ ሙከራዎች አይታጀብ እንጂ የቡድኖቹ የጨዋታ ምርጫ ታቃርኖ ጥሩ ፉክክርን አስመልክቶናል። ኳስ ከኋላ መስርቶ መውጣት ምርጫቸው የሆነው ባህር ዳሮች እንደሚጠበቀው ሁሉ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ነበራቸው። ሆኖም አዲስ አበባዎች አማካዮቻቸው እና የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ጫና በመጠቀም የተጋጣሚያቸውን የኳስ ምስረታ ሂደት ለማፈን ሲጥሩ ታይተዋል። የጣና ሞገዶቹ አማካዮች ፍፁም ዓለሙ እና ፉዓድ ፈረጃን እስከኋላ ድረስ በመከተል ቡድኑ በቀላሉ ከሜዳው እንዳይወጣ በማድረግ የመዲናዋ ቡድን አባላት መጀመሪያ አካባቢ ጥሩ ስኬትን አስመዝግበዋል።


ሆኖም አዲስ አበባዎች ከሚያስጥሏቸው ኳሶች እና በመካከለኛ ቅብብሎች መስርተው በመውጣት ወደ ግራ መስመር አጥቂያቸው ፍፁም ጥላሁን አድልተው ለማጥቃት የሞከሩባቸው ቅፅበቶች ስኬታማ አልሆኑም። በቀላሉ ኳስ ይዘው መሀል ለመሀል ጥቃት መሰንዘር የከበዳቸው ባህር ዳሮችም በሂደት የኳስ ፍሰታቸውን መጨረሻ በአዲስ አበባ ሜዳ ላይ ወደ መስመሮች እንዲያጋድል አድርገዋል። ለዚህም ቡድኑ አልፎ አልፎ ረዘም ያሉ ኳሶችን ለመጠቀም ሲገደድ አስተውለናል።

በዚህ ሂደት መሀል ላይ ባሉ ፍልሚያዎች የቀጠለው ጨዋታ 22ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝቷል። ከፍፁም ዓለሙ በረጅሙ ወደ ቀኝ የተላከውን ኳስ የመስመር ተከላካዩ መሳይ አገኘው ወደ ውስጥ ሲልከው የአዲስ አበባ መሀል ተከላካዮች መዘናጋት ታክሎበት ተመስገን ደረሰ ከመረብ አገናኝቶታል። 33ኛው ደቂቃ ላይም ፍፁም ሌላ አደገኛ ረዘም ያለ ኳስ ሳጥን ውስጥ ጥሎ ተመስገን ለማስቆጠር የሞከረበት አጋጣሚ ወደ ላይ ተነስቷል።


ቀድሞ የነበረው እንደቡድን የመከላከል ቅልጥፍናቸው በንፅፅር እየላላ የመጡት አዲስ አበባዎች ከባድ ሙከራዎች አያግኟቸው እንጂ ተጋጣሚያቸው በእነሱ ሜዳ ላይ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድ ጀምረው ነበር። የቡድኑ ብቸኛ ሙከራም በጭማሪ ደቂቃ ከአሰጋኸ ጴጥሮስ የማዕዘን ምት የተገኘ ሲሆን ኳሱ ተጨርፎ የደረሰው ዋለልኝ ገብሬ ያደረገው ሙከር ወደ ውጪ ወጥቷል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባዎች ከወገብ በላይ ሁለት ቅያሪዎች አድርገው ሲገቡ ባህር ዳሮችም አህመድ ረሺድን በማስገባት ፍፁም ዓለሙን ከአማካይነት ወደ ግራ መስመር አጥቂነት ለውጠዋል። ሲጀመር አዲስ አበባዎች በቀጥተኛ እና የቆሙ ካሶች አደጋ ለመጣል ሲሞክሩ ቢታይም ለውጥ የተደረገበት የባህር ዳር ግራ መስመር አደገኝነት ጎልቷል።51ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ኳስ ነጥቆ ያስጀመረውን ጥቃት በዚሁ አቅጣጫ በመግባት ለተመስገን ደረሰ ቢያቀብልም አጥቂው ነፃ ዕድሉን አምክኗል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ቡድኑ በድጋሚ በመሀል በኩል አጥቅቶ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። የአማካይነት ሚና ይዞ የተመለሰው ግርማ ዲሳሳ በተከላካዮች መከል የሰነጠቀለትን ኳስ ኦሴይ ማዎሊ ነበር ግብ ያደረገው።


ቀጣዮቹ ደቂቃዎችም በባህር ዳር በኩል ያለቀላቸው አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ያየንበት ሆኗል። ከቀዳሚው አጋማሽ በተለየ መሀል ለመሀል ጥቃቶችን የመሰንዘር አጋጣሚው የሰፋለት ቡድኑ በሦስት አጋጣሚዎች አጥቂዎቹን ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቷል። ተመስገን ደረሰ ጉዳት ገጥሞት ከመውጣቱ በፊት ኦሴይ ማዉሊም በሁለት አጋጣሚዎች ያለቀላቸው ዕድሎችን አግኝተው ስተዋል። ተቀይሮ የገባው አጥቂው ሳድቅ ተማምን ያማከለው የአዲስ አበባ የማጥቃት ሙከራዎች ግን ኢላማውን ወደ ጠበቀ ከባድ ሙከራ ሲቀየሩ አልታየም።


የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ኳስ ይዘው ጨዋታውን የማቀዝቅዝ አዝማሚያ ሲያሳዩ የማጥቃት ፍጥነታቸው እየቀነሰ ሄዷል። አዲስ አበባዎች በበኩላቸው ረዘም ባሉ ኳሶች እስከመጨረሻው ግብ ለማግኘት ታግለዋል። 83ኛው ደቂቅ ላይ ከግራ ወደ ቀኝ አጥቂነት የዞረው ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታው ኳስ በፋሲል ገብረሚካኤል ተይዟል። የቡድኑ ሌሎች ሙከራዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት ቢደረግም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። ይልቁንም ጨዋታው ሊያበቃ ሰከንዶች ሲቀሩ ኦሴይ ማዉሊ ተከላካዩ እያሱ ለገሰ በአግባቡ መቆጣጠር ያቃተውን ኳስ በመንጠቅ ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው በባህር ዳር 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።