ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ሲቀጥል በቀዳሚነት የሚደረገውን ጨዋታ በዳሰሳችን ቃኝተነዋል።

እንደመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ ሁለተኛው ሳምንትም ከከፍተኛ ሊግ የመጡትን ቡድኖች እርስ በእርስ ያገናኛል። የዚህ ሳምንት ባለተራዎቹ አዲስ አበባ እና አርባምንጭ ሲሆኑ ሁለቱም ውድድሩን በሽንፈት መጀመራቸው ነገ ሲገናኙ ከተከታታይ ሽንፈት ለመራቅ ብርቱ ፍልሚያ ሊያደርጉ እንደሚችል ይጠበቃል።

አርባምንጭ ከተማ በመከላከያ 1-0 የተሸነፈበት ጨዋታ የነበረው የፉክክር ደረጃ በቀዳሚው ሳምንት ከታዩት ሁሉ ከፍ ያለ ነበር። የነገውም ጨዋታ በተመሳሳይ አኳኋን ሊደረግ እንደሚችል ይገመታል። ለዚህም አንዱ ማሳያ የቡድኖቹ የጨዋታ ምርጫ ነው። አዲስ አበባ በባህር ዳር ሲሸነፍም ሆነ አርባምንጭ ለመከላከያ እጅ ሲሰጥ ሁለቱም በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ መታየታቸው አጨዋወታቸው ፍጥነት እና ጉልበት ላይ ያመዘነ እንደሆነ ይነግረናል። ምንአልባት አዲስ አበባዎች በመጀመሪያ ጨዋታቸው የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ከሜዳው ሳይወጣ ማቋረጥ ላይ ብዙ ትኩረት በማደርግ ከሚነጥቋቸው ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ ያደርጉት የነበረው ጥረት በነገው ጨዋታ ላላ ብሎ ሊቀርብ ይችል ይሆናል። ያም ቢሆን ከመጀመሪያው ተጋጣሚያቸው በተለየ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት መላክ ምርጫው የሚያደርገው አርባምንጭን ጥቃት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሳይሆን በራሳቸው ሜዳ ላይ በመግታት ጥቃትን ለማስጀመር መሞከራቸው የሚቀር አይመስልም።

የነገ ተጋጣሚዎቹ በትኩረት በኩል ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉባቸው ይታመናል። አርባምንጮች በመከላከያ የተቆጠረባቸው የተሻጋሪ ኳስ ጎል እስከዛ ደቂቃ ድረስ ለመሰል ጥቃቶች ምላሽ ይሰጡበት ከነበረበት መንገድ አንፃር ያልተጠበቀ ነበር ማለት ይቻላል። የባህር ዳርን የኳስ ፍሰት እግር በእግር እየተከታታሉ ሲያከሽፉ የነበሩት አዲስ አበቤዎችም ደቂቃዎች ሲገፉ ትኩረታቸው እየቀነስ የመጀመሪያ ግብ ሲያስተናግዱ በተመሳሳይ የመሀል ተከላካዮቻቸው ዝንጉነት ትልቅ ሚና ነበረው። በመሆኑም የትኛው ቡድን በተሻለ ሁኔታ በመከላከል ወቅት የትኩረት ደረጃውን አሻሽሎ ይመጣል የሚለው ጉዳይ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ሁለቱም አሰልጣኞች በመጀመሪያ ጨዋታቸው የኋላ ክፍላቸው ላይ ቅያሪዎችን ሲያደርጉ መመልከታችንም የዚህ ነፀብራቅ ይመሳል።

ጨዋታውን በሌላኛው የሜዳ ክፍል ስኬት ስናስበው ነገ ሁለቱም የዓመቱ የመጀመሪያ ግባቸውን ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡ መሆናቸው እናስተውላለን። ይህንን ለማድረግም ፊት መስመር ላይ በመጀመሪያው ጨዋታ ያልነበራቸውን እርጋታ ተላብሰው ወደ ሜዳ መግባት የግድ ይላቸዋል።
እንደኋላው ክፍል ሁሉ ፊት ላይም በአንደኛው ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ቅያሪዎችን ማድረጋቸውን ስናስተውልም ነገም በአጥቂዎች በኩል ለውጦቶችን እንስንጠብቅ ያደርገናል። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ወደ ግራ በፍፁም ጥላሁን በኩል አርባምንጭ ደግሞ ወደ ቀኝ ወደ አሸናፊ ኤልያስ አቅጣጫ ያመዘን የማጥቃት ሂደታቸውን ተጋማችነት መቀነስ የግብ ዕድል የሚፈጥሩበትን አጋጣሚ ቁጥር ከፍ ሊያደርግላቸው ይችላል። ከዚህ ውጪ ከሁለቱም አጨዋወት እና የመከላከል ግድፈት አንፃር በጨዋታው ተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶች ግቦችን ይዘው ሊመጡ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ይሆናል።

አዲስ አበባ ከተማ ኤልያስ አህመድ ፣ ቴዎድሮስ ሀሞ እና ዳግም በልምምድ ወቅት ሌላ ጉዳት የገጠመው ፋይሰል ሙዘሚልን ግልጋሎት አያገኝም። በመጀመሪያው ጨዋታ የልምድ እጥረት ልዩነት እንደፈጠረ ጠቁመው የነበሩት አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከሥራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ነገም ሦስቱንም የውጪ ዜጎች የማይጠቀሙ ይሆናል። በአርባምንጭ በኩል በመከላከያው ጨዋታ ጉዳት ያገኘው ሱራፌል ዳንኤል ከጨዋታው ውጪ ሲሆን ከማርቲን ኦኮሮ ውጪ ያሉት የውጪ ዜጎችም ለአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን እንደማይደርሱ ሰምተናል።

ፌደራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ኃላፊነቱን ተረክበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ነገ የሚገናኙት ከ2009 የውድድር ዓመት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በያኔው ግንኙነታቸው አንድ ጊዜ 1-1 ሲለያዩ በሌላኛው ጨዋታ አርባምንጭ 3-1 መርታት ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ወንድወሰን ገረመው

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ዘሪሁን አንሼቦ – ኢያሱ ለገሰ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ብሩክ ግርማ – ሙሉቀን አዲሱ – ያሬድ ሀሰን

እንዳለ ከበደ – ሳዲቅ ተማም – ፍፁም ጥላሁን

አርባምንጭ ከተማ (4-3-3)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደል አበበ – አሸናፊ ፊዳ – አንድነት አዳነ – መላኩ ኤልያስ

አብነት ተሾመ – አቡበከር ሸሚል – አሸናፊ ተገኝ

አሸናፊ ኤልያስ – ፀጋዬ አበራ – በላይ ገዛኸኝ