ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

ምሽት ላይ በተደረገው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማን 3-0 አሸንፏል።

ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ከተጋራበት የመጀመሪያ ጨዋታ አንፃር ፍራንሲስ ካሀታን በሀብታሙ ገዛኸኝ ምትክ አሰልፏል። ከወላይታ ድቻው ድል ሁለት ቅያሪ ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ዳንኤል ደምሴ እና አቤል እንዳለን በዳንኤል ኃይሉ እና ሱራፌል ጌታቸው ምትክ ተጠቅመዋል።

ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የተደረገበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳይቶናል። በዚህም ቡድኖቹ በሁለቱ ሳጥኖች መሀል ብርቱ ፍልሚያን ያድርጉ እንጂ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመቅረብ ሲዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። ከጅምሩ ረጅም ኳሶችን ወደ ፊት አጥቂያቸው ይገዙ ቦጋለ በመላክ አደጋ የመፍጠር ምልክት ያሳዩት ሲዳማዎች በፍሬው ሰለሞን አማካይነት ያደረጓቸው ሁለት ሙከራዎች በግቡ አግዳሚ ተመልሰዋል። በቅድሚያ ሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር አሻምቶት የተጨረፈውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ መትቶ የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመስበት 15ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ራቅ ብሎ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ላይ አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ ተመልሷል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ ድሬዎች ኳስ ይዘው ከሜዳቸው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት አጥቂዎቻቸው ጋር ሳይደርስ ይቋረጥ ነበር። የመሀል ፍልሚያውን ረዘም ባሉ ኳሶች ለማለፍ የሚያደርጉትም ጥረት ባሰቡት መጠን የግብ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣ አልነበረም። በመሆኑም የጨዋታ ሂደታቸው የተጋጣሚያቸው እንቅስቃሴ በማቋረጥ እና የግብ አጋጣሚን ባላመጡላቸው ወደ ፊት ገፍቶ ለመሄድ በሚሞክሩ ቅብቅብሎች ብቻ የተገደበ ሆኗል።

ሲዳማዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻነትም አደጋ ለመጣል ጥረዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትጉት በዳኤል ደምሴ ላይ በክርኑ ጥፋት ቢሰራም ከዳኛ እይታ ውጪ የነበረ በመሆኑ የፍሬው ሰለሞን የማዕዘን ምት ወደ መሬት ሲወርድ አግኝቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት የወጣ ነበር። ሆኖም ቡድኑ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከተሻጋሪ ኳስ ግብ አግኝቷል። አማኑኤል እንዳለ ከፍሬው የደረሰውን ኳስ ከቀኝ ሲያሻማ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርበት በነበረው የግራ መስመር ሌላኛው የመስመር ተከላካይ ሰለሞን ሀብቴ አግኝቶ በድጋሚ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ይገዙ ቦጋለ በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል።

በቅብብል ወደ ሲዳማ ሳጥን መግባት አስቸግሯቸው የቆዩት ድሬዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ በጋዲሳ መብራቴ በቀኝ በኩል ወደ ሳጥን መድረስ ችለው ነበር። ሆኖም ጋዲሳ መብራቴ ዕድሉን ወደ ግብ አጋጣሚነት ሳይቀይር ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች። ተጫዋቹ በዚህ ቅፅበት ጥፋት ተሰርቶብኛል ቢልም የዕለቱ ዳኛ በዝምታ አልፈውታል።

በቀሩት ደቂቃዎችም ሲዳማዎች ከቀጥተኛ እና የቆሙ ኳሶች አደጋ መጣል የቀጠሉበት ነበር። 40ኛው ደቂቃ ላይ ያኩቡ መሀመድ ከማዕዘን ምት ባገኘው አጋጣሚ ለግብ የቀረበበት ሙከራ በዚህ ረገድ ለግብ የቀረበው ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ድሬዎች ወደ አጥቂዎቻቸው ኳስ የማድረስ ስራውን ለማነቃቃት በሚመስል መልኩ ሱራፌል ጌታቸውን በአቤል ከበደ ለውጠው አስገብተዋል። ጨዋታው ከዐረፍት ሲመልስ ተጨማሪ አወዛጋቢ ውሳኔ ተመልክተናል። በፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጪ የተሞከረ ኳስ በድሬ ተከላካዮች ተጨረርፎ የደረሰው ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ውስጥ ሁለተኛ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎበታል። የጨዋታው የበላይነት አሁንም ወደ ሲዳማ አጋድሎ ሲቀጥል ቡድኑ 60ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ቴዎድሮስ ያሻማውን የቅጣት ምት ሄኖክ ኢሳይያስ ጨርፎት አደጋ ቢፈጥርም ፍሬው ጌታሁን እና የብርቱካናማዎቹ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል።

የሲዳማን የማጥቃት ጫና ለመከላከል ከኳስ ውጪ ወደ ራሳቸው ሜዳ የሚያዘነብሉት ድሬዎች ወደ ማጥቃት ሲሸጋገሩ አልፎ አልፎ ጥሩ ቅፅበቶችን ሲያገኙ ቢታይም በቁጥር በዝተው ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ አለመቻላቸው አደጋ ከመፍጠር አርቋቸው ቆይቷል። በቡድኑ የተሻለ አጋጣሚ 69ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ በግል ጥረቱ በግራ በኩል ሰብሮ በመግባት ያኩቡ መሀመድን አልፎ ያስቀረለትን ኳስ ሙኸዲን ሙሳ ወደ ላይ ሰዶታል።

75ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡና በፈጣን የቀኝ መስመር ጥቃት ሁለተኛ ግብ አግኝቷል። ከሀብታሙ ገዛኸኝ የተሰነጠቀለትን ኳስ መስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ በፍጥነት በመድረስ ወደ ውስጥ ሲያሳልፍለት ሳጥን ውስጥ ነፃ የነበረው እና ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ፍሬው ሰለሞን አክርሮ በመምታት ግብ አድርጎታል።

ድሬዎች ሳሙኤል ዘሪሁን እና ሄኖክ አየለን ቀይረው በማስገባት የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም 88ኛው ደቂቃ ላይ ከሄኖክ ኢሳይያስ በተነሳ ኳስ ሳሙኤል ከቅርብ ርቀት ሳይጠቀምበት ከቀረው ኳስ ሌላ አደጋ ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። ይልቁኑም በጭማሪ ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝ ያሻማውን ኳስ የሞከረው ይገዙ ተከላካዮች ሲደረቡበት በድጋሚ መትቶ በማስቆጠር ልዩነቱን አስፍቶታል። በመጨረሻም ሲዳማዎች በጨዋታው የ3-0 ባለድል መሆን ችለዋል።