ኤርትራዊው አጥቂ መቼ ወደ ሜዳ ይመለሳል?

ባህር ዳር ከተማን ዘንድሮ የተቀላቀለው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ወደ ሜዳ የሚመለስበት ጊዜ ታውቋል።

ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ባስተናገደችው የሴካፋ ውድድር ላይ ደምቆ የታየው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ውድድሩን ባስተናገደችው ከተማ ባህር ዳር ዐይን ውስጥ ገብቶ በክለቡ ለመጫወት ፊርማውን እንዳኖረ ይታወሳል። ክለቡን ዘግየት ብሎ በመቀላቀልም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከአዲሶቹ አጋሮቹ ጋር ከከወነ በኋላ በ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ጨዋታ ማድረግ ጀምሮ ነበር።

በምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ተጫዋቹ በሁለተኛው ጨዋታ ላይ ክለቡ ፋሲል ከነማን ሲገጥም ትከሻው ላይ ጉዳት አጋጥሞት ገና በስምንተኛው ደቂቃ በኪዳነማርያም ተስፋዬ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል። ጉዳቱ ጠንከር ያለ መሆኑን ተከትሎ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዳኑ ከፍተኛ የአጥንት ስፔሻሊስት የህክምና ማዕከል ክትትሉን ሲያደርግ የነበረው ተጫዋቹም የትከሻው አጥነት (ክራቪክል) መሰበሩን ተከትሎ መደገፊያ ብረት ገብቶለት የነበረ ሲሆን አሁን መጠነኛ መሻሻል በማሳየቱ ከሦስት ቀናት በፊት ብረቱ እንደወጣለት አውቀናል።

ይህ ቢሆንም ግን ተጫዋቹ ወደ ልምምድ ለመመለስ አሁንም ሁለት ሳምንታት እንደሚያስፈልጉት ለማወቅ ችለናል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ በደንብ እያገገመ መጥቶ ከቡድን አጋሮቹ ጋር መደበኛ ልምምዱን በቀጣዩቹ ሁለት ሳምንታት ሰርቶ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሮናል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና እንደ ዓሊ ሁሉ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የጣና ሞገዶቹን የተቀላቀለው ሌላኛው አጥቂ ተመስገን ደረሰ ቁርጭምጭሚቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት የሀዲያው ጨዋታ አልፎታል። የእርሱም ጉዳት ከምን ደረሰ ብለን ባጣራነው መሠረት ደግሞ ተጫዋቹ ከዚህ በኋላ ለ10 ቀናት ከልምምድ እንደሚርቅ እና ሊጉ ከእረፍት ሲመለስ ለጨዋታ ዝግጁ እንደሚሆን ተጠቁመናል።