የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-1 ወላይታ ድቻ

የሦስተኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን በምሽት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን በአዳማ ከተማ ላይ ካስመዘገበ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ያሰቡትን ስለማሳካታቸው

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው። በኳስ ቁጥጥሩ እነርሱ የተሻሉ ናቸው። እኛ ደግሞ በውጤት የተሻልን ነበርን። በመጀመርያው አርባ አምስት የፈቀድንላቸው ቦታዎች ነበሩ። የመስመር ተጫዋቾቹ በነፃነት እንዲጫወቱ ፈቅደናል ከምንከተው አጨዋወት አንፃር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ያጨዋወት ለውጥ አድርገን በአራት ሦስት ሦስት አምጥተን በስርዓት በመጫወት ተጋጣሚያችን በእኛ ሜዳ ላይ በብዙ ቁጥር እንዲገኝ አልፈቀድንለትም። ዞሮ ዞሮ እግርኳስ በአሁን ጊዜ ስሌት ይፈልጋል። የኔ ትልቁ ዓላም የቡድኑን ስነ ልቦና መመለስ ነው። ሦስተኛ ጨዋታችን ነው ከሽንፈት ነው የጀመርነው። በሁለቱ ጨዋታ ደግሞ ጥንቃቄ በተሞላበት የቡድኑን እና የደጋፊውን ስነ ልቦና የሚመልስ ውጤት ነው የምፈልገው። ሌላውን እንደርስበታለን እንደ ቡድን እንዴት ማጥቃት መከላከል እንዳለብን በዕረፍት ጊዜው የምንሰራው ይሆናል። በድጋሚ መናገር የምፈልገው በስልጠና ውስጥ ማሻሻል ያልቻልኩት በተጫዋቾቼ ላይ ያለው የመጫወት ፍላጎት በየትኛውም በቆየሁበት ክለብ ያላየሁት ነው። ጥንካሬ ፍጥነት ጉልበት የሚስተካከል ነገር ነው። በልጆቼ አሁንም ኮርቻለው። ዞሮ ዞሮ የታክቲክ ጦርነት ነበር። ለተጋጣሚያችን ክፍተት አልሰጠዋቸውም አልከፈትኩም።

በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ስለመቆየታቸው

ባሉን ተጫዋቾች ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፤ ይዘነው የገባነው አቀራረብ አምስት ሦስት ሁለት ነው። በሁለተኛው አጋማሽ በሦስት አምስት ሁለት የመስመር አጥቂዎቹ በነፃነት እንዲጫወቱ እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች አጥቂዎቻችን ረጃጅሞች ስለነበሩ እርሱን ለመጠቀም የእነርሱ ልምድ ያላቸው አማካይ ስለነበሩ እነርሱን ማሳጣት ፈልገን ነበር ይሄን አሳክተናል። በተገኙት ቀዳዳዎች ማሸነፍ አወንደምንችል ለማሳየት ሙከራ ነበር ያደረግነውያም ተሳክቶልናል። እግርኳስ ጥሩ ተጫውተ ታሸንፋለህ ጥሩ ሳትጫወት የምታሸንፍበት ነገር አለ። አሁንም ወሳኝ ሦስት ነጥብ አግኝተናል።

ስለተቆጠረው ጎል

ዳኝነቱን ለዳኞች ትተን እግርኳስ በስህተት የተሞላ ነው። ብዙ ስህተት የሰራ ተሸንፎ ይወጣል። ስህተት የቀነሱ አሸንፈው ይወጣሉ። የሆኖ ሆኖ ጎሉ ፀድቋል ስለዚህ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አግኝተናል። ለአንድ ሳምንት ለተጫዋቾቻችን እረፍት እንሰጣለን። ስንመለስ ግን ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቁን አስበን በድክመታችን ላይ ሰርተን እንመጣለን።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ጨዋታው እንዳሰቡት ስለመሆኑ

እነርሱ በደንብ ተጠቅጥቀው ይከላከሉ ስለነበረ በተቻለን መጠን ኳሱን ቀስ ብለን ከሜዳችን በመነሳት ክፍተቶችን ለመፈለግ ሞክረናል። ግን የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻልንም። ልጆቹ የሚችሉትን አድርገዋል በዬ ነው የማስበው። የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ መጣደፍ መቻኮል ሁሉም ሰው የመጨረሻ ኳስ ሰጪ ለመሆን ይሞክር ስለነበር የምንፈልገውን የግብ ዕድል እንዳንፈጥር አድርጎናል።

ግልፅ የግብ ዕድል አለመፍጠር

ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንፈልጋለን። ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ጫና ውስጥ መኖሩ ተፈጥራዊ ነው። መጀመርያም እንዳልኩት እስከ መጨረሻው ድረስ በምንፈልገው መንገድ ከሜዳችን ለመውጣት ተጫዋቾቼ ለመውጣት እየሞከሩ ነው። ግን እንዳልኩት የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ ሁሉም የመጨረሻ ኳስ ጠያቂ ስለነበር ችኮላም ይበዛበት ስለነበር። ላዛ ይመስለኛል ዕድል መፍጠር ያልቻልነው።

የተጫዋቾች ቅያሪ ስኬታማ ነበር

ጎሎችን ብናገባ ኖሮ የተሳካ ነው ተብሎ ይታሰባል። ያው ተጠቅጥቀው እየተከላከሉ ስለነበር በኳስ ክህሎታቸው የተሻሉ ልጆችን አስገብተን ክፍተቶችን ለመፈለግ ነው የሞከርነው ግን ዞሮ ዞሮ አልተሳካልንም።