ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

ነገ ከሰዓት የሚደረገውን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን በመካከላቸው አምስት የነጥብ ልዩነት ያላቸውን ክለቦች ያገናኛል። ዘንድሮ በሰንጠረዡ አናት ለመፎካከር የሚያስችል ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ባህር ዳሮች ከሁለት ጨዋታ ስድስት ነጥቦች ሰብስበው ለሦስተኛው ይቀርባሉ። ከዚህ በተለየ አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ወልቂጤዎች የአምናውን መንገድ ደግመው ላለመጓዝ ከአምስት ክለቦች ብቻ የተሻለ ደረጃቸውን በፍጥነት ለማሻሻል ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካትን በማሰብ ወደ ጨዋታው ይገባሉ።

ተጋጣሚዎቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን አግኝቶ ከቅብብሎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቀዳሚ ምርጫቸው ነው። ይህ በመሆኑ የመሀል ክፍላቸው ስኬት ጨዋታውን የመወሰን አቅም ይኖረዋል። ባህር ዳሮች በሁለተኛው ጨዋታ ሦስት የመሀል ተከላካዮችን ወደ መጥቀም ሲመጡ ምክንያቱ በመስመር ተመላላሾች መሀል ሜዳው ላይ ተጨማሪ የሰው ኃይል ለማግኘት መሆኑን አሰልጣኝ አብርሀም ጠቁመው ነበር። ይሁን እና ቡድኑ ከሜዳው ኳስ ይዞ ለመውጣት የሚያደርገው ሙከራ በሆሳዕናዎች እየታፈነ ለአደጋ የተጋለጠባቸው እና ሙከራዎችን ያስተናገደባቸው ቅፅበቶች ለነገው ጨዋታ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነጥብ ሆኖ ተመልክተነዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች ከዚህ በተለየ የመሀል ሜዳ ብልጫን አጥቂዎቻቸውን በመሳብ ለማመጣጠን ይጥራሉ። ለዚህም የፊት አጥቂው ጌታነህ ከበደን ወደ ኋላ በመመለስ ቅብብሎችን የመከወን ዝንባሌ ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን አማካይ ክፍሉ ከባህር ዳር ተመሳሳይ ቦታ ጋር ሲነፃፀር የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ደካማ ነው። አሰልጣኝ ጳውሎስ በፋሲሉ ጨዋታ በቡድናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ቢናገሩም ቡድኑ አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ማድረጉ ለዚህ ማስረጃ ሆኖ የሚቀርብ ነው።

ቡድኖቹ አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት ምልክቶችም ይታይባቸዋል። በዚህ ረገድ ወልቂጤዎች በመስመር አጥቂነት ያሬድ እና ጫላን የመሰሉ በቴክኒክ እና ሰብሮ በመግባት የተሻሉ አሊያም ፈጣን እና የተሻለ የአካል ብቅት የተላባሱት እስራኤል እና አህመድን የመሰሉ አጥቂዎች በመስመር በኩል አፈራርቀው ሲጠቀሙ ታይቷል። ጥምረቶቹ በሚፈለገው የውህደት መጠን ላይ ሆነው ባንመለከታቸውም በነገው ጨዋታ ምርጫቸው ተጋጣሚን በሜዳው ለማፈን እና ዕድሎችን ለማግኘት የሚራዳ ታታሪነትን ተላብሰው ወደ ሜዳ መግባትን ከግምት እንደሚያስገኑ ይገመታል።

ባህርዳርም በተመሳሳይ ኳስ ከመያዝ ባለፈ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ሲያስብ ይታያል በሂደቱ ወደ ግራ የሚያደላው የፍፁም ዓለሙ ሚናም ከፍተኛ ነው። ሆኖም ወልቂጤ ከተማ በተለይም በፋሲሉ ጨዋታ የተሻለ የማጥቃት አማራጩ አድርጎ የሚያስበው የግራ ወገኑ በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ መሆኑ መታየቱ ባህር ዳርም በሌላኛው ክንፍ ያለውን የማጥቃት ኃይል እንዲያጠናክር ምልክት የሚሰጥ ነው። በዚህ ረገድ ረመዳን የሱፍ ወደ ሜዳ ከተመለሰ አጠቃላይ የመሰመሩ የማጥቃት መከላከል ምልልስ ከፍ ማለቱ የሚቀር አይመስልም።

በግለሰብ ደረጃ ስንመለከት የባህር ዳሩ ኦሴ ማዉሊ ለሦስተኛ ጊዜ የቡድኑ ቁልፍ አጥቂነቱን ለማወጅ እንደሁለቱ ጨዋታዎች ሁሉ የማጥቃት ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል። የየቡድኖቻቸው የማጥቃት ሂደት ዋነኛ መሰረት የሆኑት ፍፁም ዓለሙ እና አብዱልከሪም ወርቁ እንቅስቃሴም በጨዋታው ለሚደረጉ ከባድ ሙከራዎች መነሻ መሆኑ አይቀርም። ሁለቱ ቡድኖች በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው የመፈተናቸው ነገር ዳግም ከታየም የተጫዋቾች የግል ጥረት ውጤቱን ለመቀየር ወሳኝ መሆኑ የማይቀር ነው።

ባህር ዳር ከተማ በማገገም ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ አጥቂው ዓሊ ሱለይማንን ግልጋሎት አያገኝም። ከባለፈው ጨዋታ በፊት በወለምታ የቀረው ተመስገን ደረሰም እንዲሁ የማይደርስ ሲሆን በመሀል ጉዳት ገጥሞት የነበረው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ግን መልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተሰምቷል። ዮናስ በርታ እና አቡበከር ሳኒ ደግሞ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርሱ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ናቸው። ቅጣቱን የጨረሰው ረመዳን የሱፍ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ጨዋታውን ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይበቃል ደሳለኝ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳትነት እንዲሁም ሄኖክ አክሊሉ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙባቸው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታዎች አምና ሲደረጉ በመጀመሪያው ዙር ወልቂጤ ከተማ 1-0 በሁለተኛው ዙር ደግሞ ባህርዳር ከተማ 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (3-4-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ሠለሞን ወዴሳ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል

አህመድ ረሺድ – አብዱልከሪም ኒኪማ – አለልኝ አዘነ – ግርማ ዲሳሳ

ሳለአምላክ ተገኘ – ኦሲ ማውሊ – ፍፁም ዓለሙ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ስልቪያን ግቦሆ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

እስራኤል እሸቱ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ