ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት የሳምንቱ አራተኛ ጨዋታ ይሆናል።

የሊጉን ዋንጫ አንድ አንድ ጊዜ ያነሱት የነገ ምሽት ተጋጣሚዎቹ ዘንድሮ የተለያየ ዓይነት አጀማመር አድርገዋል። አምና ባለክብር የሆነው ፋሲል ከነማ ዘንድሮም ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥቦች በመሰብሰብ ከወዲሁ በፉክክር ውስጥ ይገኛል። የ2010 ቻምፒዮኑ ጅማ ግን እንደአምናው ሁሉ አሁንም ለስጋት ሊዳርገው የሚችል አጀማመር ሲያደርግ በሊጉ ምንም ነጥብ ከሌላቸው ሦስት ክለቦች ውስጥ ተካቷል። የነገው ጨዋታ ለፋሲል በፉክክሩ ጠንክሮ የመቀጠል ለጅማ ደግሞ ነፍስ የመዝራት እንድምታ ይኖረዋል።

በፋሲል እና በጅማ መካከል የምናገኘው ዋናው ልዩነት የቡድን ውህደት ልዩነት ነው። ፋሲል ባለፉት ዓመታት እየተገነባ የመጣ ቡድን በመሆኑ ራሱን ይበልጥ ለማጠናከር ብቻ ወደ ዝውውሮች ወጥቷል። ከዚህ በተለየ ጅማ አባ ጅፋር ከግማሽ በላይ የሚሆነው ስብስቡ በሳለፍነው የዝውውር መስኮት የተገነባ ነው። ይህ ልዩነት በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ሲንፀባረቅ ነገም ተፅዕኖው የጎላ መሆኑ የሚቀር አይመስልም። ፋሲል የአደራደር ለውጥ ከማድረጉ ባለፈ አልፎ አልፎ ከጨዋታው ምት የመውጣት ምልክት ከማሳየቱ በቀር የወትሮው የማጥቃት ጠንካራ ጎኖቹ እና ከጎሉ ስህተቶች መራቁ አሁንም በቡድኑ ላይ የሚታዩ ባህሪያት ናቸው። ከዚህ አንፃር ጅማ በሁለቱ ጨዋታዎች የተለያዩ አደራደሮችን በመጠቀም ትክክለኛውን ፎርሙላ ለማግኘት በመንገድ ላይ ይመስላል። ከዚህ ውጪ የትኩረት እና የመናበብ ስህተቶች አደጋ ላይ ሲጥሉት ታዝበናል። በመሆኑም ነገ አጠቃላይ የቡድን መዋቅሩ መሰል ስህተቶችን ከማስወገድ እና ጠንቀቅ ብሎ ከመጫወት አንፃር እንደሚቃኝ ይጠበቃል።

ፋሲል ከነማ የሰዒድ ሁሴን እና ሽመክት ጉግሳ በሜዳው ቁመት የተመሰረተ የቀኝ መስመር ጥምረት ዋና የማጥቃት መሳሪያው ሆኖ ታይቷል። የተጫዋቾቹ ታታሪነት የሚጎላበት የቦታው ጥንካሬ ለግብ ዕድሎች ምንጭ ሲሆን መመልከት ችለናል። ይህ ሁኔታ በነገው ጨዋታ በሰዒድ አለመኖር ምክንያት ተፅዕኖው ቀንሶ ሊታይ ይችላል። በተቃራኒው በአራት የኋላ ተከላካዮች ሲጠቀም የተቀዛቅዞ የነበረው የግራ ወገኑ የማጥቃት ድርሻ በአምሳሉ ጥላሁን መመለስ ሊነቃቃ ይችላል። ከዚህ ውጪ በሁለቱ ድል ባደረገባቸው ጨዋታዎች በሦስትም በአራትም ተከላካዮች በሚጀምር አደራደር መጠቀሙ ተገማችነቱን ሲቀንስ በተቃራኒ የሚገጥመው ቡድንም እንዲሁ በሦስት ተከላካዮች ከጀመረ ከእስካሁኖቹ ሁለቱ የሚለይ በመሆኑ በምን መልኩ ምላሽ ይሰጣል የሚለው ነጥብ ተጠባቂ ይሆናል።

ጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ 1-0 በተሸነፈባቸው ጨዋታዎች በሊጋችን ደረጃ አንፃር ቁጥራቸው ብዙ የማያስከፉ የመጨረሻ የግብ ዕድሎች ፈጥሮ ተመልክተነውል። ከነገ ተጋጣሚው አንፃር እነዚህን ዕድሎች በቁጥር ማሳደግ ዋና ፈተናው ቢሆንም የፊት መስመር የአጨራረስ ሂደቱ ግን ጥያቄን ያስነሳል። የአሰልጣኝ አሸናፊ ዋና ምርጫ የሆኑት የዳዊት ፍቃዱ እና መሀመድኑር ናስር የልምድ እና ወጣት ጥምረት በዚህ ጨዋታ በተሻለ ብቃት የመጨረሻ ውሳኔዎችን መወሰን ለነገው ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዮቹም በራስ መተማመኑን ከመገንባት አንፃር እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ እንደ በላይ አባይነህ ዓይነት ጥሩ መቺዎች ያሉት በመሆኑ ከቆሙ ኳሶችም ግቦችን የማግኘት አማራጭ ይኖረዋል። ተጋጣሚው ፋሲል በጨዋታ ሂደት መሀል ላይ የሚታይበትን መቀዛቀዝ እና በጉዳት የሚያጣተቸው ተጫዋቾች ክፍተት ተጠቅሞ ግብ ለማግኘትም መሰል ጠንካራ ጎኖች ለጅማ ጥሩ ዕድል ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን አምና የተላለፈበትን የሁለት ጨዋታ ቅጣት በመጨረሱ ወደ ሜዳ ሲመለስ በሆሳዕናው ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው ሰዒድ ሁሴን እና ሱራፌል ዳኛቸው ለነገ አይደርሱም። ከዚህ በተጨማሪ ቀላል ልምምድ የጀመረው ይሁን እንዳሻው እና ኦኪኪ አፎላቢም ወደ ሜዳ እንደማይመለሱ ሰምተናል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ግን የዳዊት እስጢፋኖስ ቅጣት እንዳለ ሆኖ የመስመር ተጫዋቹ ኢዮብ ዓለማየሁ ጨዋታው በጉዳት ያመልጠዋል።

ጨዋታው በአሸብር ሰቦቃ ዋና ዳኝነት ሲካሄድ ዳንኤል ጥበቡ እና ሙስጠፋ መኪ ረዳቶች ባህሩ ተካ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በቡድኖቹ የእስካሁኑ የሊግ ግንኙነት ውስጥ ፋሲል ከነማ ሙሉ የበላይነት አለው። ከስድስት ጨዋታዎች አራቱን ፋሲል ሲያሸንፍ ሁለቱ ያለግብ ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ ፋሲል ከነማ 13 ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ 2 ግቦች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (3-4-3)

ሚኬል ሳማኬ

አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ

አብዱልከሪም መሀመድ – ሀብታሙ ተከስተ – በዛብህ መለዮ – አምሳሉ ጥላሁን

ሽመክት ጉግሳ – ፍቃዱ ዓለሙ – በረከት ደስታ

ጅማ አባጅፋ (3-5-2)

ታምራት ዳኜ

አሳሪ አልመሀዲ – በላይ ዓባይነህ – ያብስራ ሙሉጌታ

ሽመልስ ተገኝ – ሱራፌል ዐወል – ተስፋዬ መላኩ – መስዑድ መሐመድ – አስናቀ ሞገስ

ዳዊት ፍቃዱ – መሐመድኑር ናስር