ሪፖርት | ፈረሰኞቹ እና ብርቱካናማዎቹ በሰከንዶች ልዩነት በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ተጋርተዋል

የሦስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

በሁለተኛ ሳምንት በሲዳማ ቡና የተረቱት ድሬዳዋዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ፍልሚያ ሦስት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ሚኪያስ ካሳሁንን በመሐመድ አብዱለጢፍ፣ አብዱርሀማን ሙባረክን በማማዱ ሲዲቤ እንዲሁም አቤል ከበደን በአውዱ ናፊዩ ለውጠዋል። ተጠባቂውን የሸገር ደርቢ በበላይነት ያጠናቀቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ሁለት ለውጦችን ብቻ አድርገዋል። በለውጦቹም ከነዓን ማርክነህ እና ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ በደስታ ደሙ እና ቻርለስ ሉክዋጎ ተተክተዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ተሽለው የታዩት ድሬዳዋዎች በተለይ በመስመር ላይ ጥቃቶችን ለመፍጠር ቢሞክሩም አስደንጋጭ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። በአንፃሩ ቀስ እያሉ ወደ ጨዋታው ለመግባት የሞከሩት ጊዮርጊሶች በ11ኛው ደቂቃ ግዙፉ አጥቂያቸው ኢማኑኤል ኦሮ አጎሮ ወደ ግራ ባዘነበለ የሳጥኑ ክፍል ባገኘው ኳስ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ግን ድሬዳዋዎች እጅግ ለግብ የቀረቡበትን ኳስ በመሐመድ አብዱለጢፍ አማካኝነት ፈጥረው የግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ አምክኖባቸዋል።


የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኢማኑኤል ኦሮ አጎሮን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች በመላክ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። ይህንን አጨዋወት ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቢሞክሩም ፍሬያማ የሆኑት በመጨረሻው የአጋማሹ ደቂቃ ነው። በዚህም አጥቂው ከጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ምኞት ደበበ የላከውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ተረጋግቶ ወደ ግራ እግሩ በማመቻቸት የመታው ኳስ በፍሬው መረብ ላይ አርፏል። ድራማ የተሞላበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጊዮርጊስን መሪ ባደረገ በሰከንዶች ውስጥ ደግሞ ድሬዳዋን ባለ ግብ አድርጓል። መሪነት የተወሰደባቸው ድሬዳዋዎች እንቅስቃሴው በቀጥታ ከመሃል ሜዳ ሲጀመር የተመታው ኳስ ጋዲሳ ጋር ደርሶት ወደ ጎል ሲመታው ማማዱ ሲዲቤ አግኝቶት ታግሎ አስቆጥሮታል።

እጅግ ቀዝቃዛ የነበረው የሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ አንድም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስተናግድ ቀጥሏል። እርግጥ ቡድኖቹ የማጥቃት ሀይላቸውን ለማጠናከር የፊት መስመራቸው ላይ ለውጦችን ቢያደርጉም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውጤታማ አልነበሩም። በአንፃራዊነት ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ አርዝመው በጨዋታው ሲንቀሳቀሱ ሲታይ ድሬዳዋዎች ደግሞ በአመዛኙ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ቁመታሙን አጥቂ ማማዱ ሲዲቤን ያማከለ የመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶች ሲልኩ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይም ጊዮርጊስ መሪነቱም ዳግም ለማግኘት ታትሮ ቢንቀሳቀስም ሳይሳላለት ጨዋታው ያለ ተጨማሪ ግብ 1-1 ተጠናቋል። በውጤቱ መሠረት ድሬዳዋ ከተማ አንድ ነጥብ ማከሉን ተከትሎ በጊዜያዊነት ከ11 ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ5 ነጥቦች ያለበት 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።