ሙጂብ ቃሲም የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል

የአልጄሪያውን ክለብ ጄኤስ ካቢሌ ከወር በፊት የተቀላቀለው ሙጂብ ቃሲም በዛሬው ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታውን አከናውኗል።

ባሳለፍነው ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከፍ ያደረገው ግዙፉ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም ውዝግብ ከተሞላበት የዝውውር ሂደት በኋላ የአልጄሪያውን ክለብ ጄኤስ ካቢሌ በይፋ እንደተቀላቀለ ይታወሳል። ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ተጫዋቾቹ በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይም የጨዋታ ጊዜ አግኝቶ ነበር። ዛሬ ደግሞ ቡድኑ ጄኤስ ካቢሌ የመጀመሪያ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብሩን ወደ ሜዲያ ከተማ አምርቶ ከኦሊምፒክ ሜዲያ ጋር ባደረገው የሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ሲለያይ ሙጂብ ቃሲም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል።

የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ በጊዜው ያላከናወነው ካቢሌ ከሦስት ቀናት በፊት ከኤስሲ ሴቲፍ ጋር በተመሳሳይ ያለ ግብ አቻ ተለያይተው ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ ግን ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም በጨዋታው ላይ አልተሳተፈም ነበር።

በተያያዘ በግብፁ ኤል ጎውና እየተጫወተ የሚገኘው ሽመልስ በቀለ ለአዲሱ ክለቡ ሁለተኛ ጨዋታውን ከትናንት በስቲያ አድርጓል። ከሽመልስ የቀድሞ ክለብ ለልመቃሳ ጋር የተደረገውና በለል መቃሳ 2-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ የብሔራዊ ቡድናችን አማካይ ለ64 ደቂቃዎች መጫወት ችሏል።