ባህር ዳር ከተማ 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮቹንም ውል አድሷል

ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ዓመት ያደገው ባህር ዳር ከተማ 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የነባሮቹን ውል በማደስ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱንም በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል።

በአሠልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ የሚመራው የባህር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን በ2013 የውድድር ዓመት ጠንካራ ብቃቱን በማሳየት ከሁለተኛው ዲቪዚዮን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉ ይታወሳል። መስከረም 12 የአሠልጣኟን ውል ለተጨማሪ ዓመት ያደሰው ክለቡ አሁን ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር አስገብቶ 10 አዳዲስ ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ማስፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የግብ ዘቧ ሽብሬ ካምቦን (መከላከያ) ጨምሮ ተከላካዮቹ አዳነች ጌታቸው (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)፣ ገነት ኃይለሚካኤል (ሀዋሳ ከተማ)፣ በላይነሽ ልንገርህ (ጌዲዮ ዲላ) እና አስራት (ልደታ) እንዲሁም አማካዮቹ ሜላት ደመቀ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) እና ሜላት ንጉሴን (ላፍቶ) አካቶ አጥቂዎቹ ትደግ ፍሰሃ (አቃቂ ቃሊቲ)፣ ሳባ ኃይለሚካኤል (ጌዲዮ ዲላ) እና ምስር ኢብራሂም (ሀዋሳ ከተማ) በአዲስ መልክ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ከተጠቀሱት አስር ተጫዋቾች በተጨማሪም ከባህር ዳር አካባቢ ካለ ፕሮጀክት የተገኘችው ታዳጊዋ ጥሩሠው ደሳለኝም ክለቡን መቀላቀሏ ተመላክቷል።

ከአስሩ አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ ደግሞ ቡድኑ ወደ ዋናው ሊግ እንዲያድግ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል አፀደ በላይነህ (ግብ ጠባቂ)፣ ዮርዳኖስ አረጋ (ተከላካይ)፣ ባንቺአየሁ ደመላሽ (ግብ ጠባቂ)፣ ሊዲያ ጌትነት (አጥቂ)፣ ጥሩወርቅ ወዳጆ (ተከላካይ)፣ ቤተልሄም ግዛቸው (አማካይ)፣ ትዕግስት ወርቄ (አጥቂ)፣ መንደሪን ታደሠ (አማካይ)፣ ቅድስት ደበበ (አማካይ)፣ ቃልኪዳን ተስፋዬ (ተከላካይ)፣ ቅድስት አባይነህ (ተከላካይ)፣ ቤዛዊት መንግስቴ (ተከላካይ)፣ ፍቅርተ ካሳ (አማካይ) እና ዝናሽ ደሳለኝን (ተከላካይ) ውል ለተጨማሪ ዓመት ማደሱ ተረጋግጧል።

ከላይ የተጠቀሱትን ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ የቀላቀለው ክለቡ በቀጣዩ ሳምንት ኅዳር 1 ባህር ዳር ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚጀምርም ተጠቁሟል።