ድሬዳዋ ከተማ ከማልያ ስፖንሰሩ ጋር ይፋዊ ስምምነት ሊፈፅም ነው

ከቅርብ ጊዜዓት ወዲህ ወደ እግርኳሱ ብቅ በማለት በአጋርነት እየሠራ የሚገኘው ኤልአውቶ ግሩፕ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ይፋዊ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ሊያከናውን ነው።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር የወንዶች ብሔራዊ ቡድንን ስፖንሰር በማድረግ በዓመት 7 ሚሊዮን ብር በገንዘብ፣ በዓመት ሁለት የTaxiye መኪኖችን ለማበርከት እና በዓመቱ ዋልያዎቹ ውጤታማ እንቅስቃሴ ላሳዬ (በተመልካቾች ለሚመረጥ) አንድ ተጫዋች የመኪና ሽልማት ለመስጠት እንዲሁም ብሔራዊ ቡድኑ ባሸነፈ ቁጥር ማበረታቻ ለማበርከት ለአራት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት መፈፀሙ ይታወቃል።

አሁን ደግሞ ወደ ክለቦች ጎራ በማለት ድሬደዋ ከተማን በተለያዩ ዘርፎች ከአስር ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ለሁለት ዓመት የሚቆይ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ለመፈፀም ከስምምነት በመድረስ ድሬደዋ ከተማ የሚጫወትበት መለያ ላይ ድርጅቱን ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ እያስተዋወቀ ይገኛል።

የሁለቱ አካላት ስምምነት ይፋዊ በሆነ መልኩ ነገ ጥቅምት 27 በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ራስ ሆቴል ከዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ የከተማው ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፥ የካቢኔ አባላት እና የኤልአውቶ ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት በደማቅ ስነ ሥርዓት የሚካሄድ ይሆናል።

ከስፖንሰርሺፑ ስምምነት በተጨማሪ ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ”ጎፈሬ” ለክለቡ የመጫወቻ መለያ እና ለደጋፊዎች በሚያቀርበው መለያዎች ዙርያ ይፋዊ ስምምነት ነገ የሚፈፅሙ መሆኑ ታውቋል።

ሶከር ኢትዮጵያም በነገው ዕለት የሚኖረውን ይህን ሥነ ስርዓት አጠቃላይ ኩነት ወደ እናንተ የምታደርስ መሆኑን ከወዲሁ ታሳውቃለች።