አዲስ አበባ ከተማ አሠልጣኙን ለማሰናበት ውሳኔ አሳልፏል

አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ ከሜዳ ውጪ በተፈጠረ ጉዳይ አሠልጣኙን ማሰናበቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በ2013 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሁለት 51 ነጥቦችን በመሰብሰብ ዳግም ወደ ሀገራችን ከፍተኛው የሊግ እርከን ያደገው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ የመክፈቻ ሦስት ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወቃል። ይህ የሜዳ ላይ ውጤቱ እንዳለ ሆኖ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የተደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ዋና አሠልጣኙ እስማኤል አቡበከር እና የቡድን መሪው ሲሳይ ተረፈ በገቡበት እሰጣ-ገባ አሠልጣኙ ቡድን መሪውን “በቡጢ መማታቸውን” ክለቡ ጠቅሶ የእግድ ውሳኔ መወሰኑ ይታወሳል።

ከእግዱ በኋላ የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለን ጨምሮ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የተለያዩ ማጣራቶችን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን ሁለቱንም አካላት አዲስ አበባ ድረስ ጠርቶ ጉዳዩን ሲመረምር ነበር። የክለቡ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አገኘሁት ባለው ማስረጃ መሠረት እስከ ጥቅምት 30 (2014) ድረስ ውል የነበራቸው አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከክለቡ እንዱሰናበቱ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህንን ተከትሎም የክለቡ ቦርድ በቅርቡ አዲስ አሠልጣኝ ለመቅጠር እንቅስቃሴ እንዲጀመር አቅጣጫ ማስቀመጡ ተመላክቷል።