የአርሰናሉ አማካይ አሁንም ዋልያዎቹን አይገጥምም

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ጋና ጨዋታ ለሀገሩ ግልጋሎት ያልሰጠው ቶማስ ፖርቴ ከሀሙሱ ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተሰምቷል።

ለ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ በምድብ 7 ተደልድለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። ምንም እንኳን በምድቡ ዚምባቡዌ እና ኢትዮጵያ ከወዲሁ መውደቃቸውን ቢያረጋግጡም የምድብ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታቸውን የፊታችን ሀሙስ እና እሁድ ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ለሚጠብቀው ፍልሚያ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የዋልያዎቹ የመጀመሪያ ተጋጣሚ የጋና ብሔራዊ ቡድንም ከሦስት ቀናት በፊት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበ መሆኑን ዘግበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ቡድኑ ወሳኝ አማካዩ ቶማስ ፓርቴን በጉዳት ማጣቱ ተሰምቷል። አይደክሜው አማካይ ጋና በሜዳዋ ኢትዮጵያን ስታስተናግድ በተመሳሳይ ጉዳት አስተናግዶ ሳይሰለፍ ቀርቶ የነበረ ሲሆን አሁንም የብሽሽት ጉዳት ማስተናገዱን የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ቡድናቸው ከዋትፎርድ ጋር ጨዋታ ከማድረጉ በፊት ለስካይ ስፖርት ተናግረዋል። አሠልጣኙ ጨምረውም ተጫዋቹ ሀሙስ በልምምድ ሜዳ ጉዳት ማስተናገዱን አመላክተው በአሁኑ ሰዓት እረፍት እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች አልፈውት ከዛም ከዚምባቡዌ ጋር በተደረጉት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ተሰልፎ የነበረው ፓርቴ ወሳኝ ጎል ማስቆጠሩም አይዘነጋም። ጉዳዩን በተመለከተ ግን የጋና እግርኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን ያወጣው መረጃ የለም።