የዋልያዎቹ አሠልጣኝ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

👉”ጨዋታዎቹ የእኛ ማለፍ እና አለማለፍ ላይ ምንም የሚያመጡት ነገር ባይኖርም በፌር ፕሌይ ማንምም ቡድን በማይጎዳ እና በማይጠቅም መንገድ እናደርጋቸዋለን”

👉”እኔ በማሸነፍ ውስጥም ሆነ በመሸነፍ ውስጥ ምን ለማድረግ ሞክረናል የሚለውን ነገር ነው የማየው”

👉”ተጫዋቾች ወድቀው ሲነሱ ጠርሙስ ላይ የወደቁ እስኪመስል ድረስ ነው የሚጎዱት”

👉”ቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ነገር ታሳቢ እናደርጋለን…”

👉”ሀገሪቷ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር አልሰማሁም ማለት አይቻልም”

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችን በሦስት ቀናት ልዩነት ከጋና እና ዚምባቡዌ ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለፍልሚያዎቹ ከጥቅምት 24 ጀምሮ ሲዘጋጅ ነበር። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ስለ ተጫዋቾች ምርጫው፣ ዝግጅቱ እና ከፊታቸው ስላለባቸው ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ከሰዓት ወሎ ሠፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

ለ40 ደቂቃዎች በቆየው መግለጫ ላይ አሠልጣኙ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች ተንተርሰው ተከታዩን ሀሳብ በመስጠት ንግግራቸውን ጀምረዋል።

“በውድድር ውስጥ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ አስሮች ውስጥ ለመግባት አስበን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ማጣሪያው ከአፍሪካ ዋንጫው በፊት ስለነበር ልምድ ለማግኘት እንድንጠቀምበት አስበን ነበር። እንዳያችሁት ምድባችን ጠንካራ ነው። ሦስቱም ቡድኖች ከእኛ የተሻሉ ናቸው። ይህ ቢሆንም ከመጀመሪያው የጋና ጨዋታ ጀምሮ የተሻለ ነገር ለማሳየት ሞክረናል። በመጀመሪያው ጨዋታ ከጋና ጋር ተጫውተን በተወሰነ ስህተት ተሸንፈናል። ከዛም በሜዳችን ከደቡብ አፍሪካ ጋር በሰራናቸው ጥቃቅን ስህተቶች ተሸንፈናል። በመልሱ ጨዋታ ደግሞ የተሻለ ነገር በማሳየት ብንቀሳቀስም ተሸንፈን አስፈላጊውን ነጥብ ሳናገኝ ቀርተናል። በዚህም ከውድድሩ ውጪ ሆነናል።”

ቡድናችን ከቀን ቀን በደንብ እየተሻሻለ ነው ያሉት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከምድቡ ቀድመው ወድቀው ዋና ዓላማቸውን ሳያሳኩ ቢቀሩም ሁለቱን ቀሪ ጨዋታዎች ግን በትኩረት እንደሚቀርቡት አመላክተዋል።

“ቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ነገር ታሳቢ እናረጋለን። ጨዋታዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫው በፊት የሚደረጉ ጠንካራ ፍልሚያዎች ስለሆነ ትክክለኛ አቋማችንን ለማየት በጥሩ ሁኔታ እንቀርባቸዋለን። ሌላኛው ደግሞ በወቅታዊ ወርሀዊ ደረጃ መንሸራተት ስለገጠመን ይህንን ደረጃ ለማሻሻል እንጠቀምበታልን።

“ጨዋታዎቹ የእኛ ማለፍ እና አለማለፍ ላይ ምንም የሚያመጡት ነገር ባይኖርም በፌር ፕሌይ ማንምም ቡድን በማይጎዳ እና በማይጠቅም መንገድ እናደርጋቸዋለን። እኛ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ኒጀር የሰራችውን ነገር ታቃላችሁ። ይህ ለሁሉም ትልቅ ትምህርት ነው።” ብለዋል።

ቀድመው ጥሪ ከቀረበላቸው 26 ተጫዋቾች ሱራፌል ዳኛቸው በጡንቻ ፣ ያሬድ ባየህ በብሽሽት ጉዳት፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ደግሞ በግል ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆናቸውን ያመላከቱት አሠልጣኙ ከዛም ፋሲል ገብረሚካኤል (በሀዘን) እና ሽመክት ጉግሳም (ዛሬ – በግል ጉዳይ) ከቡድኑ እንደወጡ ተናግረዋል። በግብ ዘቡ ፋሲል ምትክም ጀማል ጣሰው ጥሪ እንደቀረበለት ተናግረዋል።

በመቀጠል የተለያዩ ጉዳዮችን በተመለከተ አሠልጣኙ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ መስጠት ጀምረዋል። በቅድሚያ ከዝግጅት ጊዜ ማጠር ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጊዜ ማጠሩ ከአማራጭ እጦት እንደመጣ ነገርግን ከዚህ በኋላ ወደዚህ ዓለም አቀፋዊ አሠራር እንዲመጣ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ስለ ቡድኑ እድገት በተመለከተ ደግሞ “ከጎል ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ያገኘናቸውን ዕድሎች ለመጠቀም ጊዜ ይፈልጋል። በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ግቦች እስኪገቡብን ድረስ ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረን ነበር። ግን አልተጠቀምንባቸውም። ባለፉት 7 ጨዋታዎች የተመዘገቡትን መረጃዎች ስንመለከት ብዙ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ነበረን። ይህንን ያደረግነው ደግሞ በደረጃ ከሚሻሉን ቡድኖች ጋር ነው።

“ተጋጣሚዎቻችን ትልልቅ የጨዋታ ልምድ ያላቸው እና ትላልቅ ሊጎች ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያላቸው ናቸው። እኛ እንደ ሀገር ፕሮፌሽናል ሊግ ለመገንባት እየዳህን ነው። ፕሮፌሽናል ተጫዋችም የለንም። እኛ በጠባብ ቦታ መፍትሄ መስጠት ላይ ያለን ጉብዝና ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ ትንሽ ነገር ጨምረን የተሻለ ነገር ለመስራት እየሞከርን ነው። ቀስ እያልን ሌሎች ነገሮችን ስንጨምር ደግሞ የሚፈለገው ነገር ላይ እንደርሳለን።”

በማስከተል ቡድኑ እየተጓዘበት ስላለው መንገድ ጥያቄ ያስተናገዱት አሠልጣኙ “እኔ በማሸነፍ ውስጥም ሆነ በመሸነፍ ውስጥ ምን ለማድረግ ሞክረናል የሚለውን ነገር ነው የማየው። በወጥነት የጀመርነውን ነገር ማስኬድ ትልቅ ነገር ነው። እርግጥ የሚጎሉን ነገሮች አሉ። እነሱ ቀስ እያሉ ይመጣሉ። ስለዚህ በትክክለኛው መስመር ላይ ነን። ይህ ማለት ግን ፍፁም ነን ማለት አይደለም። በዚህ አፍሪካ ዋንጫ 5 አልያም 6 ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው የሚጫወቱበትን ዕድል ከፈጠርን ትልቅ ነገር ነው። በቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫም እየጨመርን ከሄድን የተሻለ ነገር እንገኛለን። እኔ በቦታው ለዘላለም አልቆይም። ከእኔ በኋላ የሚመጣው ሰው የተሻለ መሠረት ተገንብቶለት እንዲረከብ ማረግም ትልቅ ነገር ነው።”

በተያያዘ ከኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሦስት ሳምንታት ጨዋታዎች ጋር በተንተራሰ ከብዙሃን መገናኛ ጥያቄ ቀርቦ አሠልጣኙ ውድድሩ እየተደረገበት ያለውን ሜዳ አጣጥለው ለተጫዋቾችም ሆነ ለእነሱ አስቸጋሪ ነገር እንዳመጣ ሲናገሩ ተደምጧል።

“የሊጉ ጨዋታዎች እየተደረገበት ያለው ሜዳ አስቸጋሪ ነው። እኛ ለምንፈልገው ጨዋታም ምርጫ ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ሀዋሳ ላይ ውድድሩ ተጀምሯል። ቀጣይ አስተናጋጅ ከተሞች ግን ከሀዋሳ ትምህርት በመውሰድ የመጫወቻ ሜዳውን ማስተካከል አለባቸው። ተጫዋቾች ኳስ ማቀበል እና መቀበል የማይችሉበት ሜዳ ነው። እንዲሁም ወድቀው ሲነሱ ጠርሙስ ላይ የወደቁ እስኪመስል ድረስ ነው የሚጎዱት።”

ከሀገራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከቀረበላቸው የመጨረሻ ጥያቄ በፊት ደግሞ የጋናን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ ማድረጋቸው ተጠቃሚ እንደማያደርጋቸው ተናግረዋል። “እኛ በሀገራችን ብንጫወት ደስ ይለናል። ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። ምንም ጥያቄ የለውም ከጋና እና ከእኛ ጋና አድቫንቴጅ አግኝታለች። ምክንያቱም ሁለቱንም ጨዋታዎች በሜዳችን ስላላደረግን። ግን ይህ አንድ ጨዋታ ነው። ከዚህ በኋላ ግን ነገሮችን በቶሎ አስተካክለን ጨዋታዎችን ወደ ሜዳችን መመለስ አለብን።”

“ሀገሪቷ ላይ እየሆነ ያለውን ነገር አልሰማሁም ማለት አይቻልም። እኛም የዚሁ ነገር አካል ነን። እንደ ሀገር የሚሰማን ነገር ቢኖርም በቀጥታ የተሰጠንን ሀላፊነት ለመስራት ዝግጁ ነን። ሀገሪቷ ላይ አሁን ያለው ነገር ቻሌንጅ አይደለም ማለት አይቻልም። እየተደረገ ያለው ጦርነት እራሱ ከሌላ ሀገር ጋር አይደለም። ሁላችንም በዚህ ነገር ተጠቂ ነን። ግን በተሰማራንበት ስራ የአቅማችንን ለማድረግ ሙሉ ተነሳሽነቱ አለን።” በማለት የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ አገባደዋል።