በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በፈረሰኞቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ትላንት ምሽት በድንገተኛ የመኪና አደጋ ከዚህ አለም በሞት የተለየው ተክለወልድ ፍቃዱን ለማሰብ በ1 ደቂቃ የህሊና ፀሎት ጨዋታው የተጀመረ ሲሆን የመጀመርያው 45 ብዙም የግብ እግሎች ያልተፈጠሩበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ56 እና 62ኛው ደቂቃ አጥቂዎቹ አዳነ ግርማ እና ብሪያን ኡሞኒ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-0 መምራት ችለዋል፡፡ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ የመታት ቅጣት ምት በተከላካዮች ተጨርፋ ግብ ሆናለች፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ ሲዳማዎች ጫና ፈጥረው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡
ድሉን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን ከሲዳማ ቡና እኩል 35 በማድረስ በግብ ልዩነት መሪነቱን ተረክቧል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አስተያታቸውን የሰጡት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚፈልጉትን እንዳሳኩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በመጀመርያው አጋማሽ ሲዳማዎች አፈግፍገው በመጫወታቸው እንደፈለግን መጫወት አልቻልንም፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻለ ተንቀሳቅሰን ግብ ማስቆጠር ችለናል፡፡ ይህንን ጨዋታ ማሸነፋችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ከፊታችን ከባድ ጨዋታዎች ይጠብቁናል፡፡ ዛሬ ባናሸንፍ ኖሮ የነጥብ ልዩነታችን ሰፍቶ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንገባ ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ቀይረን የገባነው ሲስተም ጨዋታውን እንድናሸንፍ ሙሉ ለሙሉ ረድቶናል ብዬ አላስብም፡፡ የተጫዋቾቼ የማሸነፍ ስሜት ጥሩ መሆኑ ለድላችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው የመከላከል ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈላቸውና ወደ መመሪነት መመለሳቸው እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡ ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነበር፡፡ የነጥብ ልዩነታችንን ለማስጠበቅ አስበን በመምጣታችን ቢያንስ የአቻ ውጤትይዘን ለመመለስ ተጫውተናል፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ በፈጠርናቸው ስህተቶች የፈጠርናቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ከግቦቹ በኋላ ሲስተማችንን ቀይረን ለማጥቃት ሞክረናል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ባይሳካም አንድ ግብ ማስቆጠር ችለናል፡፡ ዛሬ ብንሸነፍም በሌሎቹ ቡድኖች ጨዋታ የሚፈጠረውን ውጤት ተጠቅመን ወደ መሪነት እንደምንመለስ አምናለሁ፡፡