ሸገር ደርቢ ፡ ‹‹ ሊጉ ባስገራሚ ትዕይንቶች የተሞላና የማይገመት ነው ›› ብሪያን ኡሞኒ

በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስ የከተማ ባላንጣው ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ከካምፓላ ሲቲ ከወራት በፊት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ብሪያን ኡሞኒም አንዷን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ዩጋንዳዊው አጥቂ ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ስደርቢው እና ሊጉ ተናግሯል፡፡ ‹‹ በጨዋታው እና በውጤቱ እጅግ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በመጀመርያ የደርቢ ጨዋታዬ ግብ በማስቆጠሬም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ እና ጥሩ ቡድን ነው፡፡ እነሱን ማሸነፋችን ታላቅ ነገር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ወሳኝ የነበረው ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፉና በሊጉ መሪነት መቀጠሉ ነው፡፡ ››

ለቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን 3 የሊግ ግቦች ከመረብ ያሳረፈው የቀድሞው የአዛም እና ካምፓላ ሲቲ አጥቂ ከታንዛንያው ክለብ ጋር ያሳካውን የሊግ ድል በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያም ስለመድገም ያልማል፡፡

‹‹ አሁን የሊጉ መሪ ነን፡፡ እቅዳችንም የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነው፡፡ ዋንጫውን ለማንሳት በየእለቱ ጠንካረን እየሰራን ነው፡፡ ›› ሲል የሊግ ዋንጫ ለማግኘት እየሰሩ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በመጨረሻም ሊጉን ከተጫወተባቸው ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሊጎች ጋር ያነፃፅራል፡፡ ‹‹ የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግን ጠንካራ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ በዋንጫው ፉክክር ውስጥ በርካታ ክለቦች ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ሊጉ ባልተጠበቁ ትእይንቶች የተሞላ እና የማይገመት ሊግ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ ››

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *