የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ አዳማ ከነማ ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ተጠግቷል፡፡
በውድድር ዘመኑ አጋማሽ አዳማን የተቀላቀለው ዮናታን ከበደ በ42ኛው ደቂቃ የአዳማ ከነማን ወሳኝ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ከጨዋታው በኋላ የአዳማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አንድነታቸው ለድል እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ የህብረት አጨዋወታችን ለውጤት አብቅቶናል፡፡ ስንከላከልም ሆነ ስናጠቃ የቁጥር ብልጫ እንወስዳለን፡፡ የቡና ጠንካራ ክፍል የሆነው የመሃል ክፍሉን በመዝጋትና ከአጥቂዎቻችን ጋር ሲነፃፀሩ ፍጥነት ላይ ደካማ የነበሩት ተከላካዮቻቸውን ለመብለጥ አቅደን ተሳክቶልናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የቡናው አንዋር በበኩላቸው የስነ-ልቡና አለመረጋጋት ለሽንፈታቸው መንስኤ መሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ ለጨዋታው ያደረግነው ዝግጅት መልካም ነበር፡፡ ተጫዋቾቻን በተከታታይ መሸነፋችን የፈጠረባቸው የስነ-ልቡና ችግር ጨዋታውን እንዳናሸንፍ አድርጎናል፡፡ ተጋጣሚያችን ከኛ የተሻለ ጨዋታውን የማሸነፍ ተነሳሽነት ነበራቸው፡፡ ›› ስሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አዳማ ከና ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 34 በማድረስ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በ28 ነጥብ 7 ደረጃ ላይ ረግቷል፡፡
ሊጉ ነገ እና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ነገ አዲስ አበባ ላይ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ እሁድ ደግሞ ሙገር ቅዱስ ጊዮርጊስን (09፡00) ፣ ዳሽን ወልድያን (09፡00) ፣ ሲዳማ ቡና ሃዋሳ ከነማን (09፡00) ፣ መከላከያ ወላይታ ድቻን (11፡30) ሲያስተናግዱ ንግድ ባንክ ከደደቢትም (09፡00) ሌላው የእሁድ መርሃ ግብር ነው፡፡