በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከነማን 1-0 አሸንፎ ከወራጅ ስጋት በመጠኑ የሚያላቅቀውን ወሳኝ 3 ነጥብ አሳክቷል፡፡
የኤሌክትሪክን ብቸኛ የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ቀዮቹን የተቀላቀለው ሰውረን ኦልሪስ ሲሆን ለግቧ መቆጠር የአርባንጪ ግብ ጠባቂ አንተነህ መሳ ስህተት ጉልህ ድርሻ አበርክታለች፡፡
አርበንጮች በሁለተኛው አጋማሽ የፍፁም ቅታት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም አማኑኤል ጎበና የመታውን ኳስ አብርሀም ይርጉ አክሽፎበታል፡፡
ከጨዋታው በኋላ የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ አባተ አስፈላጊውን ነጥብ እንዳሳኩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ውጤቱ ለኛ በጣም አስፈላጊያችን ነበር፡፡ አርበንጭ ከነማ ጠንካራና በፈላጎት የሚጫወት ቡድን በመሆኑ በአጨዋወታቸው ጫና ውስጥ ሊከቱን ሞክረዋል፡፡ ይህንን ጨዋታ ማሸነፋችን በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ እንድንል ከመርደቱም በላይ በጫና ውስጥ ለነበሩት ተጫዋቾቻችንም ትልቅ መነቃቃት ይፈጥርብናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአርባምንጩ አለማየሁ አባይነህ በበኩላቸው ‹‹ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ኤሌክትሪኮች ሰአት ሲያባክኑ የእለቱ አርቢትር ካሳየው ቸልተኝነት ውጪ ጨዋታው በእንቅስቃሴም ሆነ በዳኝነቱ መልካም ነበር፡፡ አላማችን በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ሆኖ ማጠናቀቅ ሳይሆን ያለፉት አመታት ውጤቶቻችንን ዘንድሮ አሻሽሎ መጨረስ ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡