ፕሪሚየር ሊግ : የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጦች (ሚያዝያ)

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተካሂደዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው ያለፉትን 4 ሳምንታት ኮከቦች መርጣለች፡፡ የሚያዝያ ወሩ የኮከቦች ዝርዝርን የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከነማ እና ደደቢት ተጫዋቾች ተቆጣጥረውታል፡፡

ግብ ጠባቂ

ፌቮ ኢማኑኤል

ናይጄርያዊው ግብ ጠባቂ ዘንድሮ ወጥ አቋም ይዞ ቀርቧል፡፡ ከፊት ለፊቱ ጠንከራ ተከላካዮች በመኖራቸው ያን ያህል ባይፈተንም ግብ የሚሆኑ ኳሶች የሚያድንበት እና ቡድኑ ጫና ውስጥ ሲገባ የሚያረጋጋበት መንገድ መልካም ነው፡፡

ተከላካዮች

አይዛክ ኢዜንዴ

ዩጋንዳዊው ተከላካይ እምብዛም ስህተት ሲሰራ የማይታይ እና ታታሪ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 4 ጨዋታዎች 10 ነጥብ ሲያገኝ የኋላ ክፍሉን በብቃት የመራው አይዛክ ነው፡፡

ዲሚጥሮስ ወልደስላሴ

የቀድሞው የሀረር ሲቲ ተከላካይ የአዳማ ከነማ ጥንካሬ የሆነው የተከላካይ ክፍል አካል ነው፡፡ አዳማ ከጠንካራ ቡድኖች ነጥቦችን የሚሰበስብበትን የመከላከል ጥንካሬ የተላበሰው በዲሚጥሮስ እና ጓደኞቹ ብቃት ነው፡፡

አስቻለው ታመነ

ወጣቱ ተከላካይ ዘንድሮ የደደቢት ቋሚ ተሰላፊነቱን አስከብሯል፡፡ ከተጣማሪው አዳሙ ሞሃመድ ጋር ድንቅ ጥምረት የፈጠረ ሲሆን በየጊዜውም መሻሻል እያሳየ ነው፡፡

 

አማካዮች

ዮናታን ከበደ

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ዳሽን ቢራን ለቆ አዳማን ከተቀላቀለ ወዲህ ምርጥ አቋሙን እያበረከተ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ሲዳማ ፣ ድቻ ፣ መከላከያ እና ቡናን ሲያሸንፍ የዮናታን ግቦች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡

ተስፋዬ አለባቸው

ጠንካራው የተከላካይ አማካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል ጥንካሬ መሰረት ነው፡፡ ለተከላካዮች ሽፋን ሲሰጥና አጣማሪዎቹ በነፃነት በማጥቃት እንቅስቀሴ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ በኩል ድንቅ ነው፡፡

ምንተስኖት አዳነ

ላለፉት ጥቂት አመታት እንደተስፈኛ ተጫዋች ይታይ የነበረው ምንተስኖት አሁን ከቅደስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ ሆኗል፡፡ ከአማካይ ስፍረ እየተነሰ ወሳኝ ግቦች ያስቆጠረ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ተሳትፎ መልካም ነው፡፡

በኃይሉ አሰፋ

ዘንድሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የቱሳን ያህል ግሩም ግልጋሎት ያበረከተ ተጫዋች የለም፡፡ የመስመር አማካዩ ለአመዛኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግቦች መቆጠር ወሰኙን ድርሻ ተወጥቷል፡፡

አጥቂዎች

ሳሚ ሳኑሚ

የሶከር ኢትዮጵያ የመጀመርያው ወር ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ሳኑሚ ወደ ድንቅ ብቃቱ ተመልሷል፡፡ ቡድኑ መከላከያን ፣ ባንክን እና ቡናን ሲያሸንፍ ከተቆጠሩ 7 ግቦች መካከል 4 በማስቆጠር ወሳኝነቱን አሳይቷል፡፡

ተመስገን ተክሌ

ሀዋሳ ከነማ ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ውስጥ እንደ ተስፋ የሚታየው የተመስገን ግብ የማስቆጠር ችሎታ መሻሻል ነው፡፡ ዘንድሮ 7 ግቦችን በሊጉ ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ወር ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ ግቦችን ያስቆጠረው የቀድሞ የደደቢት አጥቂ ነው፡፡

ብሪያን ኡሞኒ

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ዩጋንዳዊ በፍጥነት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ጋር ተላምዷል፡፡ ጊዮርጊስ ሲዳማ ፣ ኢት/ቡና እና ሙገርን ሲያሸንፍ የብሪያን ግቦች አስፈልገውታል፡፡

የሚያዝያ ወር ኮከብ ተጫዋች – በኃይሉ አሰፋ

በኃይሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት እንቅስቃሴ መሰረት ነው፡፡ ፈጣሪ ተጫዋቾች በሌሉበት የፈረሰኞቹ የመሃል ክፍልም የግብ እድሎች በሙሉ የሚገኙት በበኃይሉ በኩል ነው፡፡ የመስመር አማካዩ የሚያሻግራቸው ኳሶች ትክክለኝነት አስገራሚ ነው፡፡

የሚያዝያ ወር ኮከብ አሰልጣኝ – አሸናፊ በቀለ

ከብሄራዊ ሊግ ያደገው አዳማ ከነማ ከ21 ሳምንታት በኋላ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለው ያሰቡ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ቡድኑ በአሸናፊ በቀለ እየተመራ ጠንካራ የመከላከል እና ከሌሎች የሊጉ ክለቦች የተሸለ የቡድን ውህደት ታይቶበታል፡፡ በዚህ ወር አዳማ ያደረጋቸውን 4ቱንም ጨዋታዎች በሙሉ ለማሸነፉ ተጠቃሹ አሰልጣኙ ናቸው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *