በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና 4 ተጫዋቾችን አግዷል፡፡ የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት አራቱ ተጫዋቾች ሙሴ ገ/ኪዳን ፣ ሚልዮን በየነ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ሮቤል ግርማ ሲሆኑ ምክንያቱ ደግሞ በአቋም መውረድ እና የቡድኑን የቡድ መንፈስ በማወክ ምክንያት ነው፡፡
ተጫዋቾቹ ክለቡ ባለፈው አርብ እለት በአዳማ ከነማ 1-0 ሲሸነፍ ወደ ሜዳ ያለገቡ ሲሆን ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ አንዋር ያሲን ተጫዋቾቹ ያልተሰለፉት በጉዳት ምክንያት እንደሆነ ገልፆ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሚልዮን በየነ ያልተሰለፉት በጉዳት ሳይሆን ክለቡ ውሳኔውን በማሳለፉ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
አቶ ሙሉጌታ አያይዘውም ‹‹ ተጫዋቾቹ ከክለቡ ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ በመሆኑ የሚለወጥ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እስካለኝ መረጃ ድረስ ግን አራቱ ተጫዋቾች በእገዳው ምክንያት ልምምድ መስራት አቁመዋል፡፡ ›› ብለዋል፡፡