ፕሪሚር ሊግ ፡ ደደቢት እና ሳኑሚ በድንቅ አቋማቸው ቀጥለዋል

 

ዛሬ በተካሄደ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት ኤሌክትሪክን 4-0 በማሸነፍ 2ኛ ደረጃን ከሲዳማ ተረክቧል፡፡

ደደቢት 4-0 ባሸነፈበት የእለቱ ግጥሚያ ሳሙኤል ሳኑሚ በቀድሞ ክለቡ ላይ 3 ግቦች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ታደለ መንገሻ ቀሪዋን አንድ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሳኑሚ ዛሬ ያቆጠራቸውን 3 ግቦች ጨምሮ በሊጉ 18 ግቦች በማስቆጠር ከፊሊፕ ዳውዚ በ3 ግቦች ርቆ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን መምራቱን ቀጥሏል፡፡

ደደቢት ድሉን ተከትሎ ጨዋታውን ነገ የሚያደርገው ሲዳማ ቡናን ቀድሞ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ከመውረድ ስጋት በመጠኑ ተላቆ ነበረው ኤሌክትሪክ ደግሞ በድጋሚ የመውረድ ስጋት ፊቱ ተደቅኗል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የደደቢቱ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀኃዬ ጨዋታው ከጠበቁት በታች እንደቀለላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ሁልጊዜም ተዘጋጅተን የምንመጣው አሸንፈን ለመውጣት ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ኤሌክትሪክ ከገመትነው በታች ቀላል ተጋጣሚ ሆኖልናል፡፡ ሳኑሚ በየጨዋታው ግቦች በማስቆጠር ለክለባችን ውጤታማነት ቁልፍ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ ››

የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ በበኩላቸው ደደቢት ማሸነፍ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡ ‹‹ ደደቢት ሙሉውን የጨዋታ ክፍለጊዜ በልጠውን ተጫውተዋል፡፡ ስለዚህም አሸንፈውናል፡፡ በግብ ጠባቂው ስህተት ግብ በመቆጠሩ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ጠባቂ ለመቀየር ተገደናል፡፡ ነገር ግን ደደቢቶች የተሻሉ ስለነበሩ ለውጥ መፍጠር አልቻልንም፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታ ተጫዋቾቼ ጉልበታቸውን ጨርሰው ከ3 ቀን በኋላ መጫወታቸውም ለሽንፈታችን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ››

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *