‹‹ ቻምፒዮንነት ለእኔ ሁሌም አዲስ ነው ›› አዳነ ግርማ

በቅርቡ ራሱን ከብሄራዊ ቡድን ያገለለው አዳነ ግርማ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር ላሳየው ከፍተኛ መሻሻል ተጠቃሽ ተጫዋች ነው፡፡ በወሳኝ ጨዋታዎች ግቦችን አስቆጥሮም ፈረሰኞቹን በድጋሚ ለሊግ ቻምፒዮንነት መርቷል፡፡

ግዙፉ አጥቂ ትላንት ምሽት የዋንጫ ባለቤትነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ ለጋዜጠኞች የሰጠውን አስተያየት እነዲህ አቅርነዋል፡፡

ስለ ወቅታዊ አቋሙ

ጥሩ የውድድር ዘመን አሳልፌያለሁ፡፡ በተለይ 2ኛው ዙር ላይ ላሳየሁት መሻሻል አሰልጣኝ ፋሲል እና ዘሪሁን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የየእለት ልምምዴን በአግባቡ ሲከታተሉ እና ጠንካራ ልምምድ ሲያሰሩ ነበር፡፡

 

ከብሄራዊ ቡድን ራሱን ስለማግለሉ

ራሴን ከብሄራዊ ቡድን ማግለል የፈለግኩት ለወጣቶች ቦታዬን ለመልቀቅ ነው፡፡ ላለፉት 10 አመታት ለብሄራዊ ቡድን ተጫውቻለሁ፡፡ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ፡፡ በዚህም ፍፁም ደስተኛ ነኝ፡፡

 

ስለ ደጋፊዎቻቸው

ደጋፊዎቻችን ከአዲስ አበባ በርቀት በሚገኙ እስከ ወልድያ እና ጎንደር ባሉ ከተሞችም እየተገኙ ሲያበረታቱን ነበር፡፡ ለደጋፊያችን ይህ ዋንጫ ሲያንሰው ነው፡፡

 

ስለ 80ኛ አመት አላማቸው

80ኛ አመታችንን በድል ጀምረናል፡፡ በቀጣዩ አመት ለምንሳተፍበት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግም ጠንካራ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በፊት በኮንፌድሬሽን ዋንጫ 8 ውስጥ መግባት ችለናል፡፡ በቀጣዩ አመት አላማችን በቻምፒዮንስ ሊጉ 4 ውስጥ ለመግባት ነው፡፡

 

በተደጋጋሚ ዋንጫዎችን ስለማሸነፉ

በርካታ ዋንጫዎችን ባሸንፍም ቻምፒዮንነት ለእኔ ሁሌም አዲስ ነው፡፡ የተፈጠርኩት አሸናፊ ለመሆን ነው፡፡ በእግርኳስ ህይወቴን ያሳለፍኩትም አሸናፊ በሆኑ ክለቦች ውስጥ ነው፡፡ (ከሀዋሳ ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 9 የሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል)

 

ስለ በኃይሉ አሰፋ

በኃይሉ ፍፁም ልዩ የሆነ አመት አሳልፏል፡፡ የቡድን ተጫዋች ነው ፤ በርካታ ለግብ የሚሆኑ ኳሶች አቀብሏል ፤ ለቡድኑ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል፡፡ የዘንድሮው ኮከብነት ለሱ ይገባዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *