ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ ሲያስፈርም አንጋፋዋን ተጫዋች ወደ አሰልጣኞች ቡድን ቀላቅሏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተወዳዳሪ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ ሲያስፈርም የነባር አሰልጣኞችን ውል በማደስ ተጨማሪ አሰልጣኝ ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቀው ሀዋሳ ከተማ ከወራቶች በፊት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ያስፈረመ ሲሆን አሁን ደግሞ የመጨረሻ ፈራሚ አድርጎ ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩን የግሉ አድርጓል። የቀድሞዋ የደደቢት እና መቐለ 70 እንደርታ ግብ ጠባቂ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ንግድ ባንክን በመቀላቀል ክለቡ በዚህ ዓመት በኬኒያ እስካደረገው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ውስጥ ቆይታን ካደረገች በኋላ ለሀዋሳ ከተማ የአንድ ዓመት ቆይታን ለማድረግ ፊርማዋን አኑራለች፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረጅም ጊዜ በመጫወት የምትታወቀዋ እና እስከተጠናቀቀው ዓመት ድረስ ስትጫወት የነበረችው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ አስናቀች ትቤሶ የተጫዋችነት ህይወቷን በማገባደድ የሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ቡድኑን ተቀላቅላለች፡፡ ቡድኑ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል የነበራቸውን የዋና አሰልጣኙ መልካሙ ታፈረ እና ረዳቱ በልጉዳ ዲላን ኮንትራት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ያራዘመ ሲሆን ክለቡም ለ2014 የውድድር ዘመን ዝግጅቱን አጠናክሮ መሥራቱን ቀጥሏል፡፡