ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ በተጎዳችው ዓባይነሽ ኤርቄሎ ምትክ አዲስ ግብ ጠባቂ አስፈረመ

መከላከያ ዓባይነሽ ኤርቄሎ በጉዳት በዚህ ዓመት በሜዳ ላይ የማንመለከታት በመሆኑ በምትኩ አዲስ ግብ ጠባቂ የግሉ አድርጓል፡፡

በመቶ አለቃ ስለሺ ገመቹ የሚመራው እና በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ላይ ጠንካራ ተፎካካሪው መከላከያ ከወራት በፊት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል ከሰሞኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በይፋ ጀምሯል፡፡ ቡድኑ ካስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች መካከል አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽ ኤርቄሎ በሀዋሳ ከተማ በ2013 የውድድር ዘመን በጨዋታ ላይ የገጠማት ጉዳት በአዲሱ ክለቧም በማገርሸቱ እና ተጨማሪ ህክምና የሚያስፈልጋት በመሆኑ ዘንድሮ ለፈረመችለት የጦሩ እንስቶች ስብስብ ግልጋሎት የማትሰጥ ይሆናል፡፡ የተጫዋቿን ግልጋሎት እንደማያገኝ የተረዳው ክለቡም በምትኩ አዲስ ግብ ጠባቂ አስፈርሟል፡፡ የቀድሞዋ የወላይታ ድቻ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታን ያደረገችው ትዕግስት አበራ ናት በምትኩ መከላከያን የተቀላቀለችው፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከአራት አመታት የሀዋሳ ከተማ ቆይተዋ ዘንድሮ ለሁለት አመት ለመጫወት መከላከያን ተቀላቅላ የነበረችው ፈጣኗ አጥቂ መሳይ ተመስገን ከሆርሞን አለመመጣጠን ጋር በተያያዘ እንዳትጫወት ውሳኔ የተላለፈባት በመሆኑ ከቡድኑ ጋር የማንመለከታት መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡