ከፍተኛ ሊግ | ንግድ ባንክ በአዲስ መልክ በ25 ተጫዋቾች ቡድኑን አዋቅሮ ዝግጅቱን ጀምሯል

በአዲስ መልክ የተቋቋመውና አሠልጣኝ ደጋረገ ይግዛውን የቀጠረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 25 ተጫዋቾችን በማስፈረም ዝግጅቱን ሲጀምር በዛሬው ዕለትም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ አሸንፏል።

ከአራት ዓመታት በፊት ከዋናው የሀገሪቱ ሊግ ወደ ሁለተኛው እርከን ሲወርድ እንዲፈርስ የተደረገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአራት ዓመታት በኋላ በአመራሮቹ መልካም ፈቃድ ወደ ውድድር ለመግባት በከፍተኛ ሊጉ የሚወዳደረውን ኢኮሥኮ ወደ ራሱ ማዞሩ ይታወሳል። በመቀጠልም አሠልጣኝ ደጋረገ ይግዛው በአንድ ዓመት ውል የቀጠረው ክለቡ ወዲያው ወደ ተጫዋቾች ዝውውር በመግባት 25 ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን አዋቅሯል።

ከፈራሚዎቹ መካከል አመዛኞቹ የከፍተኛ ሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ሲሆኑ እንደ ከድር ኸይረዲን (ከጅማ አባ ጅፋር)፣ ያሬድ ዘውድነህ (ከድሬዳዋ ከተማ)፣ ብርሃኑ ቦጋለ (ከመድን)፣ ይስሃቅ መኩርያ እና ሄኖክ ገምቴሳ (ከድሬዳዋ ከተማ) ያሉት ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ሲጫወቱ የምናውቃቸው ተጫዋቾች ናቸው። ለረጅም ጊዜያት በምክትል አሰልጣኝነት እንዲሁም በ2009 ከአጋማሹ ጀምሮ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት በክለቡ ሰርቶ የነበረው አሠልጣኝ ሲሳይ ከበደን ምክትል እንዲሁም ንጉሤ ወልደአማኑኤልን የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ያደረጉት አሠልጣኝ ደጋረገ ክለቡ ከዞረበት ኢኮሥኮ አምስት ተጫዋቾችን ጨምሮ ከሥር የተዘረዘሩትን ተጫዋቾች አስፈርመዋል።

ግብ ጠባቂዎች የራስወርቅ ተረፈ፣ ጌታሁን አማረ እና ሞናለ በቀለ ሲሆኑ ተከላካዮች ደግሞ ከድር ኸይረዲን፣ ያሬድ ዘውድነህ፣ ዘሪሁን አብይ፣ ታደለ ባይሳ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ አቤኔዘር ኦቴ፣ ሳሙኤል ወንድሙ እና ብሩክ ግርማ ናቸው። (የተከላካዮች ምስል ከላይ ተያይዟል)

አማካይ ክፍሉ ላይ ይስሐቅ መኩሪያ፣ ሔኖክ አውሎ፣ አባይነህ ፊኖ፣ ሚካኤል ዳኛቸው፣ ናትናኤል ወርቁ፣ ሔኖክ ገምቴሳ እና ደሳለኝ ወርቁ ቡድኑን ሲቀላቀሉ የመስመር እና የፊት አጥቂ ቦታ ላይ ደግሞ የኋላሸት ሰለሞን፣ ዮሐንስ ኪሮስ፣ ኢሳይያስ ታደሠ፣ አዳም አባስ፣ ሰለሞን ጌታቸው፣ አብዱልሰላም የሱፍ እና ውብሸት ካሣዬ ፈርመዋል።

ክለቡ ከሁለት ሳምንት በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን አዲስ አበባ ላይ መቀመጫውን በማድረግ በራሱ ሜዳ እያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውኖ 1-0 አሸንፏል።