ከፍተኛ ሊግ | ስልጤ ወራቤ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመራው የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ስልጤ ወራቤ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮቹንም ውል ማራዘም ችሏል፡፡

ከወራት በፊት በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ከሚገነቡ አሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነውን ግርማ ታደሰን በአንድ ዓመት የውል እርዝማኔ የግሉ ያደረገው በምድብ ሐ የከፍተኛ ሊግ ተካፋዩ ስልጤ ወራቤ ለ2014 የውድድር ዘመን ካለፉት ዓመታት በተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት እና ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ እቅድ ይዞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን መስራት ከጀመረ ሁለት ሳምንታትን አስቆጥሯል፡፡ ከአሰልጣኙ ጋር በሀድያ ሆሳዕና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ በረዳት አሰልጣኝነት ማገልገል የቻሉት ኢዘዲን አብደላ እና ምንተስኖት መላኩን የአሰልጣኝ ቡድን አባላት አድርጎ የቀጠረ ሲሆን አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን በተለይ ልምድ አላቸው ተብለው የሚጠበቁትን ወደ ስብስቡ አምጥቷል፡፡

ደስታ ጊቻሞ ስልጤ ወራቤን ተቀላቅሏል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን ፣ ደቡብ ፖሊስ ፣ ሀድያ ሆሳዕና ፣ ስሑል ሽረ እና ባለፈው ዓመት በአዳማ ከተማ ቆይታ የነበረው ግዙፉ ተከላካይ በደቡብ ፖሊስ እና ሀድያ ሆሳዕና አብረውት የሰሩትን አስልጣኝ ጥሪ ተቀብሎ ክለቡን መቀላቀል ችሏል፡፡

ከሲዳማ ቡና ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ ያለፉትን አምስት ዓመታት በክለቡ ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ክፍሌ ኪአ ፣ በሀድያ ሆሳዕና እና ሀምበሪቾ ዱራሜ የተጫወተው ተከላካዩ መስቀሉ ለቴቦ ፣ በድሬዳዋ ከተማ ዘለግ ላሉ ዓመታት በመጫወት ያሳለፈው አማካዩ ረመዳን ናስር፣ ድሬዳዋ ከተማን ከለቀቀ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አዲስ አበባ ከተማን በአምበልነት እየመራ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ካስቻሉ ተጫዋቾች መሀል አንዱ የነበረው አማካዩ ከድር አዩብ ፣ አውስኮድን ለቆ አምና በአዲስ አበባ ከተማ የተከላካይ አማካይ በመሆን ሲጫወት የነበረው ሰይድ ሰጠኝ ፣ በሀዋሳ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ እና ባሳለፍነው አመት በሀምበሪቾ ዱራሜ ቆይታ የነበረው አማካዩ ፀጋአብ ዮሴፍ ፣ በአጥቂ ስፍራ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ባለፈው አመት በጅማ አባጅፋር የተጫወተው ሳዲቅ ሴቾ ፣ ወደ ልጅነት ክለቡ የተመለሰው የቀድሞው የወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ጅማ አባጅፋር እና ሀምበሪቾ አጥቂ አምረላ ደልታታ ፣ ከወላይታ ድቻ የተገኘው እና በሀምበሪቾ ከአሰልጣኙ ጋር አምና ያሳለፈው አጥቂ በረከት ወንድማገኝ ፣ በደቡብ ፖሊስ ፣ ሀላባ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ የተጫወተው አጥቂው በኃይሉ ወገኔን እና ተከላካዩ ሮቦት ሰለሎ ከሀምበሪቾ ዱራሜ የክለቡ የፈረሙ አዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በዝርዝር እንዳስረዳው ከሆነ በሙከራ ከአካባቢው ስምንት ተጫዋቾችን ከሰሞኑ የግሉ ሊያደርግ መዘጋጀቱን እንዲሁም ከእነኚህም መካከል አምስት ታዳጊዎች መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ከዚህ ባለፈ በቡድኑ የነበሩ ስምንት ነባር ተጫዋቾች ውላቸው እንደታደሰላቸውም ጭምር ለማረጋገጥ ችለናል፡፡