የአንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ተራዝሟል

የ2014 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ቀደም ብሎ የተቀመጠለት የዕጣ ማውጣት እና የማስጀመሪያ ቀናት ላይ ለውጥ ተደርጎባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚዘጋጁ ውድድሮች መካከል በርካታ ክለቦችን ተሳታፊ በማድረግ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚያድጉ ክለቦችን የሚለየው የኢትዮጵያ አንደኛ ውድድር ተጠቃሹ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ከወር በፊት በገለፀው መሠረት ህዳር 9 የዕጣ ማውጣቱ መርሀግብር እንዲደረግ እና ህዳር 18 ውድድሩ እንዲጀመር በሚል ቀኖቹ ይፋ ተደርገው የነበረ ቢሆንም ክለቦች በጠየቁት የይራዘምልን ጥያቄ እንዲሁም ከምዝገባ መጓተት ጋር በተያያዘ የዕጣ ማውጫው ዕለት ህዳር 18 ሆኖ የ2014 የውድድር ዘመን ደግሞ ታህሳስ 3 በይፋ እንዲጀመር የመጨረሻ ቀን እንደተቆረጠ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በአራት የተመረጡ ከተሞች የኮቪድ 19 ህግን በጠበቀ መልኩ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የዘንድሮው ውድድር ላይ አማራ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ ክለቦች በአካባቢው በተፈጠረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ይሳተፋሉ ወይንስ አይሳተፉም ? የሚለውን ጉዳይ የብዙሃን ጥያቄ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የአንደኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ብዙዓየው ጌታቸውን ጠይቀን እንደገለፁልን ከሆነ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ የክልሉ ክለቦች ጥቂት ሆነው ቢመጡ በሽግሽግ እንዲገቡ ይደረጋል ያሉ ሲሆን ምናልባት ቁጥራቸው ከፍ ካለ ግን በአንድ ምድብ ብቻ ተደልድለው በአንድ ከተማ ላይ ውድድራቸውን እንደሚያደርጉ ሰብሳቢው ጨምረው ነግረውናል፡፡