በ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል

በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የቦትስዋናው ጨዋታ በፊት አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚደረገው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጉዞ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የፊታችን አርብ ከሜዳ ውጪ ቦትስዋናን ይገጥማል። ቡድኑ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው 35 ሜዳ የከወነ ሲሆን ከሰዓት ደግሞ ዋና አሰልጣኙ በዝግጅታቸው ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፍሬው በሴካፋው ውድድር ከነበረው የአየር ንብረት አንፃር ተጫዋቾች ፈተናውን ተቋቁመው ቻምፒዮን መሆናቸውን ሆኖም ቡድኑ አቅም የመጨረስ ምልክት አሳይቶ እንደነበር ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ በነበረው የዝግጅት ጊዜ በቀን ሁለቴ ለመስራት ታስቦ የነበር ቢሆንም የሜዳ ችግር የነበረ በመሆኑ በቀን አንድ ጊዜ በ35 ሜዳ ላይ ሲሰሩ እንደቆዩ ገልፀዋል። ለዚህም የሜዳውን ፍቃድ ለሰጡ አካላት አሰልጣኙ ምስጋና አቅርበዋል። ከዚህ ውጪ ከሴካፋው ውድድር በፊት በነበረው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ከተሳተፈው ቡድን ላይ ሁለት ሦስት ለውጦች ብቻ መደረጋቸውን እና እንደአስፈላጊነቱ አብዛኛው ስብስብ በነባር ተጫዋቾች በማሰባጠር እንደሚጠቀሙ ጠቁመዋል።

ከጋዜጠኞች በተነሱ ጥያቄዎች መነሻነት አሰልጣኙ በሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ተጋጣሚያቸውን በተወሰኑ ቪዲዮዎች ተመልክተው መገምገማቸውን ጠቁመው ከሚጠቀሟቸው ተጫዋቾች አንፃር ፎርሜሽን ሊለዋወጥ ቢችልም አሸናፊ ቡድን ይቀጥላል ብለዋል። የተጋጣሚን ሁኔታ በማየት የአጨዋወት ለውጦች እንደሚኖሩም የአሰልጣኙ ሀሳቦች ይጠቁማሉ።

ብሔራዊ ቡድኑ የሴካፋ ቻምፒዮን መሆኑ ለዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ዋስትና እንደማይሆን ለተጨዋቾቻቸው ማስገንዘባቸውን ያነሱት ዋና አሰልጣኙ ቡድናቸው በድሉ እንደማይዘናጋ ለዚህም ይበልጥ እንደሚሰሩም አስረድተዋል። በመጨረሻም በዕድሜ ዕርከን ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ የተጨዋቾች መተካካት እንዲኖር አካዳሚዎች እና ተቋማት ላይ መሰራት እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርበው መግለጫቸውን አጠናቀዋል።