ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የ5ኛ የጨዋታ ሳምንት በክለቦች ዙርያ ያተኮሩ ዓበይት ጉዳዮች የመጀመሪያ ፅሁፋችን ክፍል ናቸው።

👉 ወላይታ ድቻ ማስገረሙን ቀጥሏል

በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት በሽንፈት ሊጉን አሀዱ ያሉት ወላይታ ድቻዎች አራት ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍ አስራ ሁለት ነጥቦችን በመሰብሰብ አሁን ላይ የሊጉን አናት ለመቆናጠጥ በቅተዋል።

በክረምቱ በየትኛውም ዓይነት የቅድመ ውድድር ዝግጅቶች ላይ ባለመካፈላቸው ውድድሩ ሲጀመር ከተጫዋቾች የጨዋታ ዝግጁነት እና የቡድን ውህደት ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ጥያቄዎች ጋር ሆነው የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያ የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ጥያቄዎቹ እውነት ስለመሆናቸው ፍንጭ የሰጠ ጨዋታ ቢያደርጉም ከጨዋታ ጨዋታ ግን በዚህ ረገድ የሚታዩ መሻሻሎችን እያሳዩ ይገኛል።

በተጨማሪም በሰበታ ከተማው ጨዋታ ዳግም እንደተመለከትነው የቡድኑ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ እየተጫወቱ የሚገኝበት የፍላጎት ደረጃ በእጅጉ የሚያስገርም ነው ፤ እንደ ቡድን ሜዳ ላይ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የሚጀምሩትም ሆነ ተቀይረው ወደ ሜዳ የሚገቡ ተጫዋቾች በሙሉ ሜዳ ላይ ለቡድናቸው ያላቸውን ሰጥው የሚጫወቱበት መንገድ እጅግ የተዋጣለት ሆኗል።

ቡድኑ በሰበታ ከተማው ጨዋታ በተመራበት ቅፅበት እንኳን ውጤቱን መቀልበስ እንደሚችሉ በማመነን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አጥቅተው በመጫወት በተከታታይ ተጨማሪ ግቦችን አስቆጥረው አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ሌላው ቡድኑ በሂደት መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኝበት ጉዳይ የማጥቃት አጨዋወቱ ነው። በ2ኛ እና በ3ኛ የጨዋታ ሳምንት አንድ ግብ ብቻ አስቆጥረው ቢያሸንፉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ሦስት እንዲሁም አራት ግቦች አስቆጥረው ማሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ከቀደሙት ጨዋታዎች በተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠር መጀመራቸው የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ላይ መሻሻሎችን መመልከት ስለመጀመራችን በግልፅ ያሳያሉ።

አሁን ደግሞ ተከታዮቻቸው ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ የሊጉን መሪነት ለብቻቸው መጎናፀፋቸው የተጫዋቾችን ሥነ ልቦና በማጎልበት ረገድ ከሚኖረው አዎንታዊ ሚና አንፃር ይህ አስደናቂ ሰሞነኛ ግስጋሴያቸው የት ድረስ ይዟቸው እንደሚጓዝ የምንመለከተው ይሆናል።

👉 የፋሲል ከነማ መንገራገጭ

የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በመጀመሪያዎቹ ሦስት የጨዋታ ሳምንታት ድል በማድረግ አምና ካቆሙበት የቀጠሉ ቢመስሉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ግን ቡድኑ ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ ያስገደደ ሆነዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በአዲስአበባ ከተማ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተገደው ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ተጋጣሚው ይዞበት ለቀረበው ከፍተኛ ጫና ማምለጫ መንገድ ለማምጣት ተቸግሮ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ደምድሟል። ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሉት ከሽንፈቶቹ ባለፈ በአርባምንጩ ጨዋታ አምበላቸው ያሬድ ባየህን በሁለተኛ ቢጫ እንዲሁም ሀብታሙ ተከስተን በቀጥታ ቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል።

ብዙ ጊዜ ውጤታማ በሆኑ ቡድኖች እንደሚከተሰተው ውጤት በሚጠፉባቸው ጊዜያት የቡድኑ ተጫዋቾች ረዘም ላለ ጊዜ በማሸነፍ ሥነልቦና ውስጥ በመቆየታቸው መነሻነት በጥቂት አጋጣሚዎች ውጤት ሲጠፉ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ሥነምግባርም ጥያቄ ውስጥ ሲገባ እንመለከታለን።

በተለይም ሀብታሙ ተከስተ ባልተጠበቀ መልኩ በአዕምሮ መዛል (Frustration) በመነጨ መልኩ ወርቅይታደስ አበበን በክርን የተማታበት እንዲሁም አምሳሉ ጥላሁን እና ሽመክት ጉግሳ በአንድ አጋጣሚ በስፖርታዊ ጨዋነት መነሻነት ለተጋጣሚ የተለቀቀ ኳስን አስታከው የፈጠሩት ንትርክ በቡድኑ ውስጥ ሰሞኑን ውጤት ማጣት የፈጠረው ጫና የሚያሳይ ነው።

ቀጣዮቹም የቡድኑ መርሐግብሮች አስቸጋሪ ይመስላሉ። በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ከሰሞኑ ድንቅ ግስጋሴ ላይ የሚገኘውን ወላይታ ድቻን የሚገጥመው ቡድኑ በቀጣይ ከሲዳማ ቡና ፣ መከላከያ ፣ ባህርዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገናኝ ይሆናል።

የትኛውም ቻምፒዮን ቡድን በቀጣዩ ዓመት ክብሩን ለማስጠበቅ በተለያዩ ምክንያቶች ሲቸገር ይስተዋል። ታድያ የፋሲል ከነማ ከነማ የዚህ ዑደት ሰለባ እየሆነ ወይስ በውድድር ዘመኑ ጉዞ ላይ ሊያጋጥመው የሚችለው ያልተጠበቀ ሰሞነኛ የአቋም መዋዠቅ የሚለው ነጥብ በቀጣዩቹ ሳምንታት ይበልጥ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻም አሸንፏል

5ኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ ይጠበቅ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታዎችን ማሸነፍ ተቸግሮ በሊጉ ግርጌ አካባቢ ቆይታ ቢያደርግም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።

የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌው ስብስብ አምና በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በተነፃፃሪ ጥራት ያደረጋቸው የነበሩ ነገሮችን ዘንድሮ ለማሳደግ ተቸግሮ ቢከርምም በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያደረገው ታክቲካዊ ለውጥ ቡድኑን ለውጤት አብቅቶታል።

በመቀደሙት ጨዋታዎች እና በጅማ አባ ጊጅፋሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት ጨዋታ ቁልፍ ሰው የሆነው አቡበከር ናስር እንቅስቃሴዎችን ለመጨረስ ከሚያስችለው አቋቋም ውጪ ይበልጥ ወደ ራሱ ሜዳ እየተሳበ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ለመሆን በመገደዱ ኢትዮጵያ ቡና በመሀል ሜዳ ከሚኖረው የቁጥር ብልጫ ባለፈ ሳጥን ውስጥ ለተጋጣሚ ተከላካዮች በማጥቃት ረገድ ስጋት የሚደቅን ቡድን መሆን ሳይችል ቀርቷል።

በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አቡበከር ናስር ይበልጥ ለጎል ቀርቦ እንዲጫወት መደረጉ ለኢትዮጵያ ቡና የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ አስፈሪ ሆኖ ተመልክተነዋል። አቡበከር ወደ መሀል ሲሳብ ቡድኑ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ከጀርባ በመሮጥ እንዲሁም የጎንዮሽ እንቅስቃሴዎች አጥቶ ቢቆይም አቡበከር ይበልጥ ወደ ፊት በተገፋ ሚና መጫወቱ ተጠቃሚ አድርጓቸው ሁለት ግቦችን ከተጫዋቹ አግኝተው የመጀመሪያ ድላቸውን አሳክተዋል።

👉 በተለየ መንገድ ለመቅረብ የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች

በ5ኛ የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አመርቂ ነገሮችን ማስመልከት የተቸገረውን የማጥቃት ጨዋታቸውን ለማሻሻል ከተለመደው አቀራረባቸው የተለወጠ መንገድን ለመከተል ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

የተወሰኑ መዛነፉች (Asymmetric) የመሆን ነገሮች ቢኖሩም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ ለ3-2-4-1 የቀረበ የተጫዋቾች አደራደርን ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል። ይህ መነሻ ቅርፅ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ብዙም የሚለዋወጥ ነገሮች አልነበሩም። የሲዳማን መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለመመከት ያለመ የሚመስለው የተጫዋቾች አደራደር እና ምርጫ የጥቃት ስጋቱን በመቀነሱ ውጤታማ ነበር።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተጠቀሙት የተጫዋቾች አደራደር በራሱ እንደየትኛውም የተጫዋቾች አደራደር የሚሰጠው ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ ጎድለቶች ነበሩት። በተለይ ደግሞ በኋላ ሦስት የተከላካይነት ከጀመሩት ደስታ ደሙ ፣ ምኞት ደበበ እና ፍሪምፖንግ ሜንሱ ግራ እና ቀኝ የሚገኘውን ሰፊ የሜዳ ክፍል የመከላከል ኃላፊነት የተጣለባቸው ለመስመር ተመላላሾች(Wing Backs) ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዕለቱ ይዘውት በገቡት የመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ይህን ሚና እንዲወጡ ወደ ሜዳ ያስገቧቸው ተጫዋቾች (ከነአን ማርክነህ እና ተገኑ ተሾመ) ሚናውን ለመውጣት የተመቹ አለመሆናቸውን ተከትሎ በዚህ ረገድ በጣም አስቸጋሪ ጊዜያትን ያሳልፋሉ ተብሎ ቢገመትም የሲዳማ ቡናዎች ደካማ የማጥቃት ፍላጎት ብዙ እንዳይቸገሩ አድርጓቸዋል።

በአንፃሩ ጊዮርጊሶች ይዘውት የገቡት የተጫዋቾች አደራደር በቁጥር በርከት ብለው የተጋጣሚ ሳጥንን ለማጥቃት የሚያስችል ቢሆንም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመሄድ ያደረጉት ጥረት ብዙም ውጤታማ አልነበረም ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋቾች ለውጥ እና ከመጀመሪያው በተለይ ቀጥተኛነትን ጨምረው በመጫወት ሲዳማ ቡናን ጫና ውስጥ መክተት ችለዋል።

👉 ደጋፊዎቹን መጠቀም የተቸገረው ሲዳማ ቡና

ከአምስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ብዙ የተጠበቀባቸው ሲዳማ ቡናዎች በ6 ነጥቦች በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሊጉ ውጤታማ ቡድኖችን በመገንባት በሚታወቁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመሩ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተሻሉ ዝውውሮችን የፈፀሙት ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ የውድድር ዘመን አጀማመር ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሜዳ ላይ እያስመዘገቡ የሚገኙት ውጤት ግን ብዙም አመርቂ የሚባል አይደለም።

በሀገራችን እግርኳስ የሜዳ ላይ ተጠቃሚነት የሚለው እሳቤ እርግጥ ከአምናው የውድድር ዘመን አንስቶ ውድድሮች በተመረጡ ከተሞች ከመካሄዳቸው ጋር ተያይዞ በተወሰነ መልኩ ተፅዕኗቸው የቀነሰ ቢመስልም አሁንም ግን ደጋፊዎች ከፍ ያለ ሚና መወጣት እንደሚችሉ ይታመናል።

ሊጉ በተመረጡ ከተሞች መካሄድ ከመጀመሩ አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት በሊጉ ቡድኖች በሜዳቸው ሊገጥሟቸው ከማይፈልጓቸው ቡድኖች አንዱ የነበረው ሲዳማ ቡና በሊጉ ውጤታማ በነበረባቸው የውድድር ዘመናት ከቡድኑ የሜዳ ላይ ውጤታማነት በስተጀርባ የደጋፊዎቹ ሚና በቀላሉ የሚመጥ አይደለም።

ለዚህም ማሳያነት አምና አዲስ ግደይን ብቻ ያጣው ሲዳማ እንደ ደጋፊዎቹንም በማጣቱ ያንን የቀደመውን ሲዳማ ቡናን ለማየት ተቸግረናል። ዘንድሮ ግን በተወሰነ መልኩ ወደ ሜዳ እንዲገቡ ፈቃድ የተሰጣቸው ደጋፊዎች ቁጥር መጨመሩን እና የውድድር የመጀመሪያ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በሲዳማ ክልል ርዕሰ መዲና እንደመደረጉ ሲዳማ የተሻለ አጀማመር ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ሲሆን እየተመለከትን እንገኝም።

👉 መከላከያ ወደ አሸናፊን ተመልሷል

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባህርዳር ከተማን 2-0 በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

ለተጋጣሚው ኳስን እንዲቆጣጠር የሚፈቅደው ቡድኑ በጠጣር መከላከል እና በቀጥተኛ አጨዋወት ግቦችን ለማግኘት የሚሞክር ቡድን እንደሆነ እየተመለከትን እንገኛለን። በተለይ ደግሞ ቢኒያም በላይ በሜዳ ላይ በሚኖርባቸው ጨዋታዎች ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተለየ አድማስ ሲሰጥ ይስተዋላል።

ከጥልቀት የሚነሳው ቢኒያም ኳሶችን እየነዳ ወደ ተጋጣሚ ይዞ በመግባት (progressive carrier) ከመሆኑ ጋር በተያዘ በቀጥተኛ ኳሶች ኡኩቱ ኢማኑኤልን ለመቀጠም በሚቸገሩባቸው አጋጣሚዎች በተጨዋቹ አስደናቂ ፍጥነት እና ክህሎት በመጠቀም ኳሶችን ወደ ማጥቂያው ሲሶ ለማድረስ ሌላኛው አማራጭ ሲሆናቸው ተመልክተናል።

እንደ ቡድን ቡድኑ በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተጋጣሚ ጫና ውስጥ ሆኖ ጫናን ተቋቁሞ ለመጫወት ያላቸው ዝግጁነት አስገራሚ ሆኖ ተመልክተነዋል። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ ቢኒያም በላይ በፍፁም ቅጣት እና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ችለዋል። በድሉ ታግዘውም ነጥባቸውን ወደ አስር በማሳደግ 3ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።