ሲዳማ ቡና የዲሲፕሊን ውሳኔ ተወሰነበት

በሲዳማ ቡናን ከወራት በፊት ባገደው የህክምና ባለሙያ ዙርያ የዲሲፒሊን ውሳኔ ተወስኖበታል።

ሲዳማ ቡና የህክምና ባለሙያ (ወጌሻ) አበባው በለጠን “አስቀድሞ ባደረግነው የውል ማጣራት የእርሶ ውል ህጋዊነት ያልተከተለ በመሆኑ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከስራ የታገዱ መሆኑን እንገልፃለን” በማለት ማገዱን እና በአንፃሩ የህክምናው ባለሙያ አበባው በለጠ በበኩሉ “ያለምንም በቂ ምክንያት የቃልም የፁሑፍ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠኝ ያለ አግባብ ከሥራ ገበታዬ መታገዴ ተገቢ አይደለም” በማለት ለፌዴሬሽኑ የቅሬታ ደብዳቤ አስገብተው እንደነበረ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።

የፌዴሬሸኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የሁለቱንም አካላት አቤቱታ እና መከራከርያ ከመረመረ በኃላ ሲዳማ ቡና ወጌሻውን ወደ ሥራ እንደዲመልስ፣ ክለቡ ያልከፈለውን ደሞዝ እንዲከፍል፣ ክለቡ ይህ ውሳኔ በደረሰው በሰባት ቀን ውስጥ እንደውሳኔው እንዲፈፅም፣ ውሳኔውን የማይፈፅም ከሆነም በፕሪምየር ሊጉ እንዳይወዳደር እና ከፌዴሬሸኑ ማንኛውም ትብብር እንዳያገኝ ሲወሰን ክለቡ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳለው በውሳኔው ደብዳቤ ላይ ተያይዞ ቀርቧል።