ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በ6ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በአምስተኛው ሳምንት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠሟቸው ሰበታ እና ድሬዳዋ በቶሎ ወደ ውጤት ለመመለስ ዕድል የሚሰጣቸውን ጨዋታ እርስ በእርስ ያደርጋሉ። ሰበታ ከተማ በሦስት ነጥቦች ብቻ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተቀምጧል። እስካሁን ከድል ጋር አለመገናኘቱም በነገው ጨዋታ አሸንፎ የመውጣት ጫናው እንዲያጋድልበት የሚያደርግ ነው። ሁለት ድሎችን ያስመዘገበው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በሰንጠረዡ ወገብ የሚገኝ ሲሆን በአራተኛው ሳምንት ጅማን ሲረታ ወደነበረው የድል መንፈስ ለመመለስ የነገው ውጤት ያስፈልገዋል።

ድሬዳዋ ከተማ የእስካሁኑን ምርጥ አቋም ያሳየበት የጅማው ጨዋታ እንደመሆኑ በወቅቱ የነበሩት ጠንካራ ጎኖቹን መልሶ ማግኘት የግድ ይለዋል። በተለይም በተጋጣሚ ሳጥን አቅራቢያ የሚደረጉ ቅብብሎቹ ጥራት በሚፈለገው ልክ አለመሆን በወልቂጤው ጨዋታ እንደልቡ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር እንዲቸገር ሲያደርገው አይተናል። በሰበታ በኩልም ተመሳሳይ ችግር ይታያል ቡድኑ ለኳስ ቁጥጥር ፍላጎት ቢያሳይም በቁጥር ከፍ ያለ ተሰላፊዎቹን ወደ ግብ ክልል አቅርቦ ደጋግሞ ሰብሮ በመግባት ተደጋጋሚ የግብ ዕድልን ሲፈጥር አይታይም። ይህ መሆኑ የፊት አጥቂው በአመዛኙ ሲባክን ይታያል። ተጋጣሚዎቹ ከኳስ ጋር ብዙ ጊዜ መቆየትን መምረጣቸው ከዚህ ደካማ ጎናቸው ጋር ሲዳመር የጨዋታው አመዛኙ እንቅስቃሴ መሀል ሜዳ ላይ እንዳይገደብ ያሰጋል።

በመከላከሉ ረገድ ስንመለከተው ደግሞ ድሬዳዋ የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን። በመጨረሻው ጨዋታ ከቆመ ኳስ ብቻ ግብ ከማስተናገዱ ባለፈ ጫና ለመፍጠር በታተረባቸው አጋጣሚዎችም ራሱን ለጥቃት አላጋለጠም ነበር። የኋላ ክፍሉ ተሰላፊዎች እንደሌላው የቡድኑ ክፍሎች ሁላ አለመለዋወጣቸው ወደ ጥሩ ውህደት እየወሰዳቸው ይመስላል። በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ወጥነት የማይታይበት ሰበታ ግን በድቻው ጨዋታ በተለይ ለመልሶ ማጥቃት እጅጉን ተጋልጦ ስንመለከተው የተቆጠረበት የግብ ብዛትም ቀላል የሚባል አይደለም። ድሬዎች ምንም እንኳን ኳስ ይዘው መቆየትን ቢያዘወትሩም ለፈጣን ጥቃት የሚሆኑ ተጫዋቾች እንደመያዛቸው በዚህ ረገድ ተጋጣሚያቸውን ሊፈትኑ ይችላሉ።

ሰበታ ከተማ የአጨራረስ ችግሩ ተቀርፏል ለማለት ተደጋጋሚ ዕድሎችን ፈጥሮ መመልከት የሚጠይቅ ሲሆን አሁን ላይ ፍፁም ገብረማሪያም ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ማስቆጠሩ ለነገም ተስፋ የሚሰጠው ይመስላል። በሦስት ጨዋታዎች ግብ ያልነበረው ቡድኑ በአራተኛው አንድ በአምስተኛው ሳምንት ደግሞ ሁለት ማስቆጠሩ ጥሩ መሻሻል ቢሆንም ተጨማሪ ወጥ የግብ አዳኞችን በነገው ጨዋታ የሚፈልግ ይመስላል። በድሬ በኩልም በማማዱ ሲዲቤ ላይ የመንተራስ ምልክት ሲታይ ለኳስ ቁጥጥሩ እገዛ ማድረግ እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚታትሩት የመስመር ተሰላፊዎቹም ግብ መድፈር ሊጀምሩ እንደሚገባ ግልፅ ነው።

ሰበታ ከተማ ዱሬሳ ሹቢሳን ከጉዳት ሲመለስ ሲያገኝ መሀመድ አበራ እና አክሊሉ ዋለልኝ ግን አሁንም አላገገሙለትም። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ዳንኤል ኃይሉ እና ያሲን ጀማል ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ለፌደራል ዳኛ ተከተል ተሾመ ተሰጥቷል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ተመጣጣኝ ፉክክር ያላቸው ሁለቱ ተጋጣሚዎች እስካሁን ስምንት ጊዜ ተገናኝተው ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ በዓምናዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል። በእስካሁኑ የሊግ ታሪካቸው ሲገናኙ ሰበታ 7 ድሬዳዋ 6 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ክሪዚስቶም ንታንቢ – በኃይሉ ግርማ

ሳሙኤል ሳሊሶ – ዘላለም ኢሳይያስ – ጁኒያስ ናንጄቤ

ፍፁም ገብረማርያም

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ