ሪፖርት | ሰበታ እና ድሬዳዋ ነጥብ ተጋርተዋል

የስድስተኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል ተደርጎ ያለግብ ተጠናቋል።

ሰበታ ከተማ ከወላይታ ድቻው ሽንፈት ባደረጋቸው የአሰላለፍ ለውጦች ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑን በምንተስኔት ዓሎ ፣ በረከት ሳሙኤልን በክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስን በታፈሰ ሰረካ ፣ ዘላለም ኢሳይያስን ጁኒያስ ናንጄቤ እንዲሁም ዮናስ አቡሌን በዘካሪያስ ፍቅሬ በመተካት ወደ ሜዳ ገብቷል። በአንፃሩ በወልቂጤ ተሸንፎ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ አብዱርሀማን ሙባረክን ሀዘን በገጠመው ጋዲሳ መብራቴ ብቻ በመለወጥ ጨዋታውን ጀምሯል።

ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በጭብጨባ የሞራል ድጋፍ በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ሰበታ ከተማ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዞ በጀመረው ጨዋታ ወደ ቀኝ ያደላ ጥቃት እና ሳጥን ውስጥ የሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶችን ቢያስመለክተንም የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻለም። ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ የተሻለ ከሜዳቸው መውጣት የጀመሩት ድሬዳዎች በንፅፅር ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ወደ ሰበታ ሳጥን ሲቀርቡ የመጀመሪያውን ከባድ ሙከራም አድርገዋል። 21ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ ከቀኝ ከአብዱለጢፍ መሀመድ የደረሰውን ረዘም ያለ ኳስ በሰበታ ተከላካዮች መሀል ሆኖ በመቆጣጠር ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶትበታል። ከዚህ ቀደም ብሎ አብዱርሀማን የሞከረው ሌላ ኳስ በአንተነህ ተሳፋዬ በእጅ ተመልሷል የሚለው የቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄም ውድቅ ሆኖ ነበር።


ቀሪው የአጋማሹ እንቅስቃሴ በመሀል ሜዳ ፍልሚያዎች የተወሰነ ነበር። ቡድኖቹ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ሆነው ተጨማሪ ሙከራዎች ሳይታዩ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ አቤል ከበደ ሰበታ ደግሞ አብዱልሀቪዝ ቶፊቅን ለውጠው የጀመሩት ሁለተኛው አጋማሽም የሜዳ ላይ ግጭቶች በርከት ብለውበት ታየ እንጂ በእንቅስቃሴ የተለየ አልነበረም። በእርግጥ ድሬዳዋዎች በአብዱለጢፍ በኩል አድልተው ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሰበታዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ከቁጥር ብልጫ ጋር ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ቢያገኙም የፍፁም ገብረማሪያም ሙከራ ፍሬው ጌታሁንን የሚያስጨንቅ አልነበረም።

66ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ አራት ለአንድ ሆነው የሜዳውን አጋማሽ ማለፍ ችለው የነበሩት ሰበታዎች አጋጣሚውን አምክነውታል። ይልቁኑም ድሬዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ በግራ በኩል የገቡበት አጋጣሚ አስፈሪ የነበረ ሲሆን አብዱለጢፍ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ዘሪሁን ከቅርብ ርቀት ለመጨረስ ያደረገው ጥረት ለጥቂት በግቡ ቋሚ ስር ወጥቶበታል።

ሰበታዎች የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ደጋግማው እንደማግኘታቸው ሁሉ ድሬዳዋ ከተማዎችም ወደ ግራ አድልተው የሚፈጥሩት ጫና በተደጋሚ ታይቷል። ጨዋታው ከውሀ ዕረፍት ሲመለስ ድሬዎች ከዚያው ከግራ መስመር አብዱለጢፍ ባሻማው ኳስ ሌላ ከባድ የግብ ዕድል ፈጥረው ማማዱ ሲዲቤ እና እንየው ካሳሁን አከታትለው ቢሞክሩም ምንተስኖት ዓሎ ሊያድንባቸው ችሏል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የተጨዋቾች የግል ብቃት የተንፀባረቀባቸው ሙከራዎችን ሲያሳዩን ግብ ጠባቂዎቹ ግን እንዲገቡ አልፈቀዱም። 78ኛው ላይ ዱሬሳ ሹኒሳ መሳይ ጳውሎስን አታሎ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በፍሬው ሲመለስ ወዲያው በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ማማዱ ሲዲቤ እንዲሁ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ላይ ሳጥን ውስጥ በመግባት የመታውን ጠንካራ ኳስ ምንተስኖት አምክኗል።

ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቀርብ ረዘም ያሉ ኳሶች ወደ ሳጥን ሲላኩ ይታይ ነበር። ያም ሆኖ ቡድኖቹ ያሰቡትን የማሸነፊያ ግብ ሳያገኙ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

በውጤቱም ሰበታ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ድሬዳዋ በበኩሉ ባገኘው አንድ ነጥብ ሌሎች ጨዋታዎች እስኪደረጉ ድረስ ከ10ኛ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።