የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 ሀዋሳ ከተማ

በስድስተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

በጣም ጥሩ ነው በምፈልገው እና አድርጉልኝ ያልካቸውን አድርገውልኛል።

ውጤቱ ከማን ጥንካሬ የተገኘ ነው

በራሳችን ጠንካራ ጎን ነው ያሸነፍነው። ማድረግ የሚገባንን ነገር የተሻለ ነገር አድርገን ማግኘት የሚገባንን ውጤት አግኝተን አሸንፈን ወጥተናል

በሁለተኛው አጋማሽ ስለ መቀዛቀዝ

ተጭነን ለመጫወት ነበር ፍላጎታችን። ሆኖም የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ትንሽ ዝቅ አድርጎናል። አንድ ቡድን ጎል ሲያስቆጥር ከፍ ይላል አንደኛው ዝቅ ይላል። እነርሱ ጎል ማስቆጠራቸው ተጭነውን እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አላየሁትም እስካየው ምንም መናገር አልፈልግም። ግን ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ውጭ ነው የመሰለኝ የዳኛን ውሳኔ አከብራለው። ያው ይሄ ነው ያወረዳቸው። እኛም እድሎችን አግኝተናል፤ እስማኤል አልተጠቀመም እንጂ ጥሩ ነበርን። ወደ አሸናፊነት ሰትመጣ ያለህን ነገር ዘግተህ ነው እንጂ ዝም ብለህ ከፍተህ አይሆንም። ዘጠናውን ደቂቃ ተቀናጅተህ ካልተጫወትክ ውጤቱን አታስጠብቀውም።

የዛሬው ውጤት ትርጉም

ትልቁ ነገር ከዛሬው ጨዋታ ያገኘነው ነጥብ ከተከታታይ ጨዋታ የአቻ ውጤት በኃላ ስለሆነ አሸንፎ ወደዚህ መምጣት ትልቅ ነገር ነው። ወደ አሸነፊ ስነ ልቦና መመለስ ትልቅ ነገር ስለሆነ ይሄን ነገር ስላመጡ በጣም ደስ ብሎኛል።

ስለ አሰልጣኝ ክራምፓቲች

እኔ የምለው ምንም ነገር የለም። የእኔ ድርሻ አይደለም። እስካሁን አብረን ስንሰራ ነበር። አሁንም የተወሰነውን ስለማላቅ ምንም የምለው ነገር የለም።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

በጨዋታው ውጤት እንዳታገኙ ምክንያቱ ምድነው

አንደኛ ዳኝነት በጣም መስተካከል አለበት። በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በተለይ መለስ ብዬ ፊልሞችን ስመለከት ብዙ ነጥቦችን እየጣልን የምንገኘው በዳኞች ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ብዙ ፍፁም ቅጣት ምቶችን ስንለለከል ነው የማየው፤ ግን ቅሬታ አቅርቤ አላቅም። ዛሬ ግን ከእረፍት በኃላ በምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በሚሰሩ ጥፋቶች ኳስ ያስቆማል። ግን ቶሎ አያስጀምርም ነበር። ደጋፊው ኳስ ሊያይ ነው የመጣው እንደዚህ ያለ ነገር ሊቆም ይገባል። ሌሎች ዳኞች እርምጃ ይወስዱ ነበር፤ ካርድ ይሰጡ ነበር። ዛሬ ግን ይህ አልሆነም። ይህን ጨዋታ ይዘው የወጡት በዚህ ነው እንጂ እንዳደረግነው እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል እንደመድረሳችን ጥሩ ነበርን። ዛሬ ውጤት ያጣነው በጥቃቅን ስህተቶችን ተከላካዮቻችን ከዚህ ቀደም አብረው ያልተጫወቱ ስለሆነ በቀይ ካርድ ባለፈው ተጫዋች ስለወጣንም ያለመግባባት ችግር ክፍተት ፈጥሮብን ልንሸነፍ ችለናል። የመጀመርያው ጎልም ሁለተኛውም ጎል በዚህ መንገድ የተገኘ ነው። በዛ ላይ ጥፈት ተሰርቶብን የገቡ ጎሎች ናቸው። ብቻ በአጠቃላይ በዳኝነት ነጥብ አጥተናል።

ስለ ቡድኑ ጎል የማስቆጠር ችግር

እውነት ነው አሁንም እድሎችን እናገኛለን። ወደ ጎል እንደርሳለን የአጨራረስ ችግር ነው። አንደኛ ወጣቶች ናቸው ልምድ የላቸውም። በአጥቂ በአማካይ እንዲሁም በተከላካይ ስፍራ ላይ አንዳንድ ማስተካከል ያሉብን ነገሮች አሉ። በሁለተኛው ዙር ላይ ቡድኑን ለማጠናከር እንሰራለን።