ኢትዮጵያዊው ዳኛ በኩዌት ዕውቅናን አገኘ

የኩዌት እግርኳስ ማኅበር ለሁለት አፍሪካዊ ዳኞች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና ሲሰጣቸው በአምላክ ተሰማ አንደኛው ሆኗል፡፡

በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ከሚያስጠሩ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ ዋንኛው ነው፡፡ ከሀገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች እስከ አፍሪካ ኮንፌድሬሽን እና ቻምፒዮንስ ሊግ አልፎም በአፍሪካ ዋንጫ እና ዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ የደረሰው ይህ ዳኛ ከሰሞኑ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎችን ከመራ በኋላ የኩዌት እግር ኳስ ማኅበር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ የኩዌት ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን እንዲመራ በማለት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት አርቢትሩም ጥያቄውን ተቀብሎ መጓዙ ይታወሳል፡፡

ወደ ስፍራው ያመራው በአምላክ እንዲሁም ደግሞ ሌላኛው ጥሪ የደረሰው የቱኒዚያ ዜግነት ያለው ሀይተሀም ኪራት በኩዌት እግር ኳስ ማህበር (KFA) በትናንትናው ዕለት የክብር ሽሎማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሽልማቱንም የኩዌት እግር ኳስ ማህበር የቦርድ ዳይሬክተር ሼይኽ አህመድ አልየሱፍ አልሳባህ አበርክተዋል።

ሁለቱ ዳኞች በ3ኛ ሳምንት የሀገሪቱ ሊግ ኩዌት ኤስሲ እና አል ቃድሲያን ቅዳሜ ዕለት ያደረጉትን ጨዋታ እና በኩዌት ኤስሲ 3-0 የተጠናቀቀው ጨዋታን የመሩ ሲሆን የማኅበሩ ቦርድ ዳይሬክተርም በጨዋታው ያሳዩትን ብቃት አወድሰዋል።