የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-2 ባህር ዳር ከተማ

በስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን ከረታ በኋላ አሰልጣኞቹ ለሱፐር ስፖርት ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ጨዋታው በሰቡት መልኩ ስለመሄዱ

የመጀመርያው አጋማሽ በምናስበው መልኩ ሄዷል፤ ጥሩም ብልጫ ነበረን። ብዙ የጎል ሙከራዎች ያደረግንበት ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ግን ያገባነውን ጎል ለማስጠበቅ ልጆቹ ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ወደ ኃላ የማፈግፈግ እና ቶሎ ከሜዳችን ያለመውጣት ችግር ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ሄዷል ሁለተኛው አጋማሽ ግን በምንፈልገው መልኩ ሄዷል ማለት አንችልም።

ጅማ አስጨናቂ ቡድን ሆኖ ስለመቅረቡ

ትክክል! ቅድም መግቢያዬ ላይ እንደተናገርኩት በተደጋጋሚ የተሸነፈ ቡድን አንዷን ጨዋታ አሸንፎ ለመነሳት ነው የሚፈልገው። ጅማ በአብዛኘው ወጣቶች ናቸው። እንደ መስዑድ ያሉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እየታገዘ ያለው። ወደ ፊት እነ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ሲመለሱ ልምድ ያላቸው ከወጣቶች ጋር ከተቀናጁ ጅማ ተጋጣሚን ማስጨነቁ ብቻ ሳይሆን ወደ ማሸነፍ ደረጃ ላይ ይመጣል ብዬ አስባለው።

ፈጣን ቀጥተኛ ኳሶች ለአጥቂዎቹ ማድረስ የጨዋታው ዕቅድ ስለመሆኑ

ትክክል ነው። ምክንያቱም ጎሎች ያስፈልጉን ስለነበር ለማሸነፍ ያንን ደግሞ ተግባራዊ አድርገናል። ብዙዎቹን ባንጠቀምባቸውም።
ሁለተኛው አርባ አምስት ግን ከኃላ መስርተን ለመውጣት የነበረን ፍላጎት የወረደ ነበር። ስለዚህ የሚጣሉ ኳሶችን ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ኳሶችን መጠቀም ላይ ደካማ ነበር። ስለዚህ እዚህ ነገር ላይ በደንብ አስተካክለን እንመጣለን።

ስለ ዓሊ ሱሌይማን

ዓሊ ለተከላካዮች አስቸጋሪ ነው። አቋቋሙ ጥሩ ነው። አጨራረስ ላይም መልካም ነው። ግን ከአንድ ወር ሁለት ሳምንት በላይ መቆየት ምን ያህል ከጨዋታ ከአካል ብቃት እንደሚያርቅ የታወቀ ነው። ነገር ግን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ከሄደ ይህን ጎል የማግባቱን ሂደት ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

ደረጃቸውን ስለማሻሻላቸው እና ስለ ቀጣይ

በቀሪው ሦስት ጨዋታዎች ይሄንኑ ለማስጠበቅ ነው። ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለማሻሻልም ተንክረን እንሰራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ

እንቅስቃሴው በውጤት ካልታጀበ ትርጉም አይኖረውም። አስከፊ ሽንፈት ነው ቡድኔ እያስተናገደ ያለው። በፀጋ ከመቀበል ውጭ ምንም ማድረግ አትችልም። በውጤት የታጀመ እንቅስቃሴም አይደለም። እንደዚህ ዓይነት ቡድን ገጥሞኝ አያቅም። እንዳውም እኔ የምታወቀው የመጀመርያው ዙር ላይ በመምራት ነው የምታወቀው። በህይወት ታሪኬ እንዲህ በተከታታይ የተሸነፈ ቡድን አለ ብዬ አላስብም።

ሜዳ ላይ ስላሰቡት እና ተጫዋቾችህ ስለተገበሩት

ዛሬ ባህር ዳር ከወትሮ የተለየ አጨዋወት ነው ይዞ የቀረበው። በእኔ በኩል ልጆቼ መስጠት የሚገባቸውን ያቅማቸውን ሰርተዋል። ከአቅማቸው በላይ መጠየቅም ከባድ ነው የሚሆነው።

የተጫዋቾችን የሚና ለውጥ መንስኤው

አማራጭ ስታጣ መንገዶችን ለመዝጋት የምትጠቀምባቸው ዘዴዎች ናቸው። ለዚህ ጨዋታ ብቻ ታስቦ አይደለም። የሚኖሩብህን ክፍተቶች መቼም በጎዶሎ አትጫወትም። ክፍተቶችን ለመሞላት የምታደርገው ጥረት ነው።

ከእረፍት በፊት ስላሉ ሦስት ሳምንት ጨዋታዎች ስለሚያስቡት

ማንኛውም አሰልጣኝ ወደ ውጤት መመለስ ይፈልጋል። በዚህ መልኩ ወደ ውጤት ለመመለስ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።