ሪፖርት | ባህር ዳር ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አሳክቷል

በስድስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በዓሊ ሱለይማን ጎሎች ጅማ አባ ጅፋርን 2-0 አሸንፏል።

ጅማ አባ ጅፋር ከቡናው ሽንፈት ባደረጋቸው ለውጦች አላዛር ማርቆስን በታምራት ዳኜ ፣ ሽመልስ ተገኝን በሱራፌል ዐወል ፣ አሳሪ አልመሀዲን በተስፋዬ መላኩ እንዲሁም መሀመድ ኑር ናስርን በአድናን ረሻድ ለውጧል። በባህር ዳር በኩል በረከት ጥጋቡ እና ኦሴይ ማዉሊ ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ የተሰለፉት ፉዓድ ፈረጃ እና መሳይ አገኘሁን ተክተው ተሰልፈዋል።

ይህም ጨዋታ እንደሌሎቹ ሁሉ ለመከላከያ ሰራዊት በጭብጨባ የሞራል ድጋፍ በማድረግ ተጀምሯል። የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የማጥቃት ፍላጎት የታየበት እና ጥሩ ምልልስ የነበረው ሆኗል። በተለይም ጅማ አባ ጅፋር ባልተጠበቀ የጨዋታ ዕቅድ እንደተጋጣሚው ሁሉ ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት ያሳየው ተነሳሽነት የጨዋታውን ግለት ከፍ አድርጎታል። በጨዋታው የተደረገው የመጀመሪያ የባህር ዳር ሙከራ ግን ግብ ሆኗል። 18ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከተከላካዮች አምልጦ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ዓሊ ሱለይማን ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብነት ቀይሯል። በእንቅስቃሴው ውስጥ ኳሱን ለአለኝ ያደረሰው ኦሴይ ማዉሊ በእጅ በመነካቱ እና አለልኝ ሲያሻማው ማስመሩን ያለፈ መምሰሉ የጅማን ተሰላፊዎች ያዘናጉ ነጥቦች ነበሩ። ያም ሆኖ ጎሉ ፀድቆ ጨቃታው ቀጥሏል።

ከግቡ በኋላም ፉክክሩ በጥሩ መንገድ የቀጠለ ነበር። ባህር ዳሮች ቅብብሎችን በማቋረጥ ወደ ጅማ የግብ ክልል በፍጥነት የሚደርሱበት አጋጣሚ አስፈሪ አድርጓቸው ነበር። ቡድኑ ወደ ግብ ከቀረበባቸው ቅፅበቶች መካከል 29ኛው ደቂቃ ላይ ማዉሊ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሞክሮ አላዛር አድኖበታል። የጅማዎች ማጥቃት ወደ አደገኛ የግብ ሙከራ የተቀየረው 33ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዱላ ሙላቱ መስዑድ መሀመድ ከቀኝ ያሻምውን ኳስ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ወደ ግብ ቢልከውም ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ባህር ዳሮች ወደግብ በደረሱበት ሌላ አጋጣሚ 38ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከረጅም ርቀት ያደረገው አደገኛ ሙከራ በግብ ጠባቂው አላዛር ጥረት ድኗል። ያም ቢሆን በሽግግሮች ወቅት ካልሆነ በስተቀር በሁለቱም በኩል ከኳስ ጀርባ የመቅረት አዝማሚያ አለመታየቱ ጨዋታውን ለአይና ሳቢ አድርጎታ አጋማሹ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምርም ጨዋታው ተመሳሳይ መልክ ነበረው። ጅማዎች በነበራቸው አቀራረብ ወደ መሀል ሜዳ የተጠጋው የተከላካይ መስመራቸው በቀዳሙው አጋማሽም ለፈጣን ጥቃት ሊያጋልጣቸው ሲቃረብ ሲታይ ቆይቶ 50ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳር ሁለተኛ ግብ አግኝቷል። አብዱልከሪም ኒኪማ ከተከላካዮች ጀርባ የሰነጠቀውን ኳስ ዓሊ ሱለይማን አምልጦ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ጎል አድርጎታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ጅማዎች በእንቅስቃሴ የተሻሉ ቢሆኑም ከፊት ሲደርሱ አደጋ መፍጠር አልቻሉም። ይልቁኑም ባህር ዳሮች አሁንም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል። በተለይም 70ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ውስጥ የላከው ኳስ ተቀይሮ በገባው ፉዓድ ፈረጃ ወደ ጎልነት ሊቀየር ተቃርቦ ነበር። ከአስር ደቂቃ በኋላም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከላካዮችን አልፎ የገባው ፍፁም ያደረገው ያለቀለት ሙከራ ሀለት ግቦች ቢያስተናግድም ቡድኑን በሰፊ ግብ ከመሸነፍ በታደገው በአላዛር የተመለሰ ነበር።

የጅማዎች የሳጥን ውስጥ ደካም የቅብብል እና የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ከሙከራ አርቋቸው ቢቆይም 83ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ ቀርበው ነበር። ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በላይ አባይነህ በግንባሩ ገጭቶ ገጭቶ ፋሲል ገብረሚካኤል በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል። የጅማዎች እስከመጨረሻው ደቂቃ የዘለቀ የሞት ሽረት ትግል ጎል ማምጣት ሳይችል ጨዋታው በባህር ዳር አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ ደረጃውን ከአስር ወደ አራት ማሳደግ ችሏል።