የዋልያዎቹ አሰልጣኞች ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር ይወያያሉ

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ጋር በነገው ዕለት በሀዋሳ ይወያያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ እየተመራ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፏቸው ከምድባቸው ማለፍ ባይችሉም በጥር ወር በካሜሩን በሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳትፎ ትኬቱን መቁረጡ ይታወሳል፡፡ ከሰሞኑ ሀዋሳ የሰነበቱት እና ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ሲከታተሉ የሰነበቱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ በነገው ዕለት (ረቡዕ) አመሻሽ 11፡00 ላይ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ከአስራ ስድስቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ዋና እና ረዳት አሰልጣኞች ጋር ለመወያየት ቀጠሮ መያዙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ውይይቱ ሊካሄድ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች፣ በቀጣይ በጥር ወር ሀገራችን ተሳታፊ በምትሆንበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ዝግጅት እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ዙርያ ውይይት ለማድረግ እና ገንቢ ሀሳቦችን ለመሰብሰብ በማለም ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱን ድረ ገፃችን ተገንዝባለች፡፡