ወደ ካሜሩን ስለሚደረገው ጉዞ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሲሳይ አድርሴ ኘሮሞሽን ጋር በመሆን ወደ ካሜሩን በሚያቀኑ ደጋፊዎች ዙርያ በሸራተን አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከአንድ ወር በኃላ በ2022 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ማለፏን ተከትሎ ከታኅሣሥ 23 እስከ ጥር 29 በካሜሩን ለሚደረገው ውድድር የደጋፊዎች እና የሚዲያ አካላት ጉዞን አስመልክቶ በሸራትን አዲስ ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩ ጥላሁን እና የሲሳይ አድርሴ ኘሮሞሽን ባለቤት አቶ ሲሳይ አድርሴ ተገኝተዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ባሕሩ የኢትዮጵኣ ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለስን ተከትሎ ወደ ካሜሩን በሚኖረው ጉዞ ደጋፊዎች እና የሚዲያ አካላት በምን መልኩ እንደሚጓዙ እና በሂደቱ ምን ምን እንደሚጠበቅ ማብራርያ ለመስጠት ጋዜጣዊ መግለጫው እንደተዘጋጀ ገልፀው ይህን ለማስፈፀም ከሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን እና ከሌላ ተቋም ጋር ለመሥራት እውቅና ሰጥተናል ካሉ በኋላ አምስት መቶ ደጋፊ ይዞ ለመሄድ መታሰቡን እና በዚህ ትልቅ መድረክ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ማስተዋወቅ የሚቻልበት መድረክ እንደሚሆን እንዲሁም በምዕራባዊያን ሚድያዎች ስለ ኢትዮጵያ ያለው ምልከታ የተሳሳተ መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ ካተቱ በኃላ አቶ ሲሳይ አድርሴ በበኩላቸው ይህንን ስራ በኃላፊት ተረክበው ለመስራት አቅደው ሰፊ ጥናት እንዳጠኑ እና ደጋፊው ተበታትኖ ከሚሄድ በአንድ ቋት ተስብስቦ ለመውሰድ ከዚህ ቀደም ካላቸው ተሞክሮ በመነሳት ማሰባቸውን ተናግረዋል። አምስት መቶ ደጋፊ እና 25 የሚዲያ አካላት ለመውሰድ መታሰቡን፣ የአስር ቀን ደርሶ መልስ ለአንድ ሰው 55000 (ሃምሳ አምስት ሺህ ብር) እንደሚሆን እንዲሁም ከአስር ቀን በላይ ቆይታ ለማድረግ የብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ውጤቱ እንሚወስነው ገልፀዋል። ደጋፊዎች በሚያደርጉት ጉዞ የተጠቀሰውን ወጪ ራሳቸው የሚሸፍኑ ሲሆን 25 የሚዲያ አካላት ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን ለመውሰድ ከፌዴሬሽኑ ጋር እንደተነጋገሩ ገልፀዋል።

በመቀጠል አቶ ባህሩ ጥላሁን የአፍሪካ ዋንጫው ወደ ኳታር ይቀየራል ስለሚባለው እና ስለሚጓዙት 25 ጋዜጠኞች አመራረጥ ጨምሮ ሌሎች ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄ ልምላሽ ሰጥተዋል

” ከካፍ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው የምነገኘው። እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ሁለተኛ አማራጭ የሚባል ነገር የለም። በካፍ በኩል አንደኛም ሁለተኛም ሦስተኛም አማራጭ የለም። ሁሉም ካሜሩን እንደሚዘጋጅ ነው የሚያቀው። በዚህ በኩል ከካፍም የተሰጠ መረጃ የለም። ስለዚህ የአፍሪካ ዋንጫ በካሜሩን ይካሄዳል የሚለውን ማረጋገጫ መስጠት እችላለሁ።

” ከጋዜጠኞች ማኅበርም ሆነ የካፍ አክሪቴሽን ካላቸው ጋር ውይይቶች እናደርጋለን። በዚህ መሠረት የሚሄዱትን የምንመርጥ ይሆናል። በዘመድ በመቀራረብ የሚደረግ መረጣ እንዳይኖር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቅርበት የሚከታተለው ይሆናል።

ከምዝገባ፣ ከደጋፊዎች ማህበራት ጋር በሚኖሩ ውይይቶች፣ ከኮቪድ ፕሮቶኮል ጋር በተገናኘ ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ ሲሳይ የጉዞው ትኬት የምግብ የሆቴል በከተማው ውስጥ ለሚደረግ ትራንስፖርት እንዲሁም የስታዲየም መግቢያ በተመለከተ አስፈላጊውን ስራዎችን ወደ ስፍራው በማቅናት የማስተካከል ስራ እንደሚሰሩ ገልፀው ሀገራቸውን በቅንነት ለማገልገልም እንዳሰቡ እና በሂደት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጋራ በመወጣት የኢትዮጵያን ስም ከፍ በማድረግ ለማኩራት እንሰራለን ብለዋል።

በሁለቱ ተቋማት ስምምነት መሠረት ከሚገኘው ገቢ 50 በመቶ ድርሻ በጋራ እንደሚወስዱ ገልፀዋል። ወደ ካሜሩን መጓዝ ለሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ከወዲሁ ምዝገባ መጀራቸውንም ተናግረዋል።